ቀጥታ፡

'ፖለቲኮ ኢሮፕ' ሚዲያ ኢትዮጵያን በሚመለከት ያወጣው መረጃ የተሳሳተና በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሃቅ ያላገናዘበ ነው

ሐምሌ 28/2013(ኢዜአ) የቤልጂዬሙ 'ፖለቲኮ ኢሮፕ' ሚዲያ ኢትዮጵያን በሚመለከት ያወጣው መረጃ የተሳሳተና በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሃቅ ያላገናዘበ መሆኑን በብራስልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

የቤልጂሙ 'ፖለቲኮ ኢሮፕ' የተሰኘ ሚዲያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነሀሴ 02 ቀን  2021 የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ከቀድሞዋ ዮጎዝላቪያ ጋር በማነፃፀር ላቀረበው ጽሁፍ የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ሰጥቷል።

በብራስልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለሚዲያው በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፤ 'ባሮንስ አርሚንካ' በተሰኘ ግለሰብ ስም የወጣው ይህ ጽሁፍ በእውነት ላይ ያልተመሰረተና ፍፁም የተሳሳተ ነው።

ጸሀፊው አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ እየፈጠረ ያለውን ችግር ዩጎዝላቪያ ገጥሟት ከነበረው ቀውስ ጋር ማነፃፀሩ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ታሪካዊ እውነታ ያላገናዘበ ነው ሲልም ነው ኤምባሲው ያስታወቀው።

ኢትዮጵያዊያን በማንነታቸው ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩ እና ለሌሎች አገራትም በአብነት የሚጠቀሱ ህዝቦች መሆናቸውን የገለጸው ኤምባሲ፤ የጸኃፊው መልዕክት "ይህን ሃቅ የካደ ነው" ብሏል።

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በዜጎች መካከል ምንም ዓይነት ጥላቻ እንደሌለም እንዲሁ።

ጸኃፊው በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሃቅ ባልተገነዘበበት አግባብ ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲሁም መንግስት በህዝብ ላይ ጥቃት እያደረሰ እንደሆነ አስመስሎ ያቀረበው ጽሁፍ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ነው ኤምባሲው ለሚዲያው በላከው ደብዳቤ ያስታወቀው።

'ዘ ኤዲተር ኦፍ ፖለቲኮ ኢሮፕ' ያቀረበው ሃሳብ የአሸባሪውን ህወሃት እሳቤ የሚያንፀባርቅና ሆን ተብሎ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማሳሳት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ የሚገፋፋ መሆኑንም ኤምባሲው አጽንኦት ሰጥቷል።

ኤምባሲው አሸባሪው ህወሃት በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ  ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በፈፀመው ጥቃት መንግስትን አስገድዶ ወደ ህግ ማስከበር እንዳስገባው ገልጾ፤ በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡድኑን በሽብርተኝነት መፈረጁን አስታውቋል።

መንግስት በትግራይ ክልል የሚኖሩ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ የተናጠል ተኩስ አቁም በመወሰን ተግባራዊ እያደረገ ቢሆንም፤ አሸባሪው ቡድን ይህን በመጣስ በአጎራባች ክልሎች ጦርነት መክፈቱን ገልጿል።

'ዘ ኤዲተር ኦፍ ፖለቲኮ ኢሮፕ' ያወጣው ጽሁፍ ይህን እውነት የማያሳይና በኢትዮጵያ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና እንዲፈጠር የሚገፋፋ ነው ሲል ኤምባሲው ለሚዲያ ተቋሙ በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም