ቀጥታ፡

የትራንስፖርት ስምሪቱ ተጠቃሚውን ከግምት ያስገባ ባለመሆኑ ለተጨማሪ ወጪ እየዳረገን ነው-የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ነሀሴ 3/2010 የትራንስፖርት ስምሪቱ ተጠቃሚውን ከግምት ያስገባ ባለመሆኑ ለተጨማሪ ወጪ እየዳረጋቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አስታወቁ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር በፒያሳ፣ ሜክሲኮ፣ ካሳንቺስና አንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ምልከታ ያደረገ ሲሆን ችግሩ መኖሩንም አረጋግጧል። ሪፖርተሩ ምልከታ ባደረገባቸው ቦታዎች ላይ ያነጋገራቸው ተጠቃሚዎች እንዳሉትም የትራንስፖርት አገልግሎት በማጣት በአማካይ እስከ ሶስት ሰዓት ተሰልፈው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡት የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች እንዳስታወቁት የትራንስፖርት ስምሪቱ የተጠቃሚውን ፍላጎት ከግምት ያስገባ አይደለም ብለዋል። በተለይም ሸገር ባስ፣ አሊያንስና መሰል የትራንስፖርት አውቶቡሶች አንዳንድ ቦታዎች ላይ በብዛት ሲገኙ፤ ህዝብ በሚበዛበት ቦታዎች ላይ ደግሞ እጥረት ያለበት ሁኔታ አለ ብለዋል። በዚህም ምክንያት የህዝብ ማመላለሻ ታክሲዎች በመደበኛው ታሪፍ ከሶስት ብር የማይበልጠውን መንገድ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ አስር ብር ይጠይቃሉ ብለዋል። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን በበኩሉ ስምሪቱን ከህዘቡ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም ጥናት አስጠንቶ መጨረሱንና በአዲስ መልክ በመከለስ ወደ ተግባር ሊገባ መሆኑን አስታውቋል። የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ዕፀገነት አበበ እንዳሉት ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት በቅርቡ አዲስ ስምሪት ይደረጋል ብለዋል። ከታሪፍ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ችግር ከአሁን በፊት በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች የቀረበውን የታሪፍ ማሻሻያ ጥያቄ በአዲስ መልክ በማስተካከል መመለሱንና ማሻሻያው ከተደረገ ወዲህ ታሪፍ በሚጨምሩ አገልግሎት ሰጭዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል። ባለስልጣኑ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን ግን ትራንስፖርት ተጠቃሚው እራሱ የወጣውን የታሪፍ ህግ በማስከበር መብቱን መጠቀም እንዳለበት ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን የትራንስፖርት ችግሩን ለመፍታት ከ8 መቶ በላይ ተሽከርካሪዎች ግዥ መፈፀሙንና  እነዚህም ተሽከርካሪዎች በቀጣዩ ዓመት ወደ ስራ እንደሚገቡ መግለጫ መስጠቱ የሚታወቅ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም