በ2013 ዓ.ም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የመንግሥት ሆስፒታሎች ሽልማትና እውቅና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በ2013 ዓ.ም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የመንግሥት ሆስፒታሎች ሽልማትና እውቅና ተሰጠ
ሐምሌ 28/2013 (ኢዜአ) የ2013 ዓ.ም የሆስፒታሎች ጥምረት ጥራት መርሃ ግብር የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የመንግሥት ሆስፒታሎች ሽልማትና እውቅና ተሰጠ።
የሆስፒታሎቹ ሽልማትና የእውቅና መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመርሃ ገበሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚንስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ላለፉት አመታት የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል በሆስፒታሎች ላይ የሪፎርም ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ከተከናወኑ የለውጥ ስራዎች መካከል የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሆስፒታሎች እርስበርስ መማማርን ማጠናከር በሰው ኃይልና በግብአት እንዲደጋገፉ ማድረግ እና የተቁዋማት ምርጥ ተሞክሮ ማስፋት የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት መርሃ ግብር አላማ መሆኑን አስረድተዋል።
የጤና ተቋማት ፅዱና ጊዜውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት አጠቃላይ ለውጥ ማምጣት የሶስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት መርሃ ግብር የትኩረት መስክ መሆኑንም ተናግረዋል።
ባለፉት ሶስት አመታት በዚህ ረገድ በተሰራው ስራ ፅዱና ጊዜውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት ከነበረበት 50 በመቶ ወደ 85 በመቶ ማድረስ መቻሉንም ገልፀዋል።
በሆስፒታሎች ጥምረት ጥራት መርሃ ግብር የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የመንግሥት ሆስፒታሎች ሽልማትና እውቅና ሊሰጥ ችሏል ብለዋል።