ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የውጭ ኃይል ጣልቃ እንዲገባባት የማትፈልግና የማትፈቅድ ሀገር ናት

ሐምሌ 28/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የውጭ ኃይል ጣልቃ እንዲገባባት የማትፈልግና የማትፈቅድ ሀገር መሆኗን ባለመረዳት  የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት መጀመራቸውን የቀድሞ የአሜሪካ የኮንግረስ እጩ አቶ ቴዎድሮስ ዓለማየሁ አስታወቁ።

ዲያስፖራው ይሄንን አውቆ በቀጣይ በሀገር ላይ የሚፈጠሩ ጫናዎችን ለማርገብ ተቀናጅቶ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይኖርበታል ሲሉም ነው የጠቀሱት።

ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመተባበር ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል በውስጥም በውጭም ጫና ለማሳረፍ ሲደረጉ የነበሩ ሩጫዎችን ማርገብ እንደተቻለም ጠቁመዋል።

አቶ ቴዎድሮስ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ዲያስፖራው ቀደም ባሉት ጊዜያት በተሳሳቱ መረጃዎች በሀገር ላይ ጫናዎችን ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶችን ለመቀልበስ በጋራ ተንቀሳቅሷል።

በዚህም ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፤ጥረቱን በተሻለ ቅንጅትና ቁርጠኝነት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተባበረ ክንድ በኢትዮጵያ ላይ በተሳሳተ መረጃ ያልተገባ ጫና ለማሳደር ሲደረጉ የነበሩ ሩጫዎች በአሁኑ ወቅት እየረገቡ መምጣታቸውን አመልክተዋል።

አሜሪካን የሚያስተዳድሩ መንግስታት በሌሎች ሀገራት ላይ ጣልቃ ሲገቡ ማየት የተለመደ ተግባር እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ሊቢያ፣ ግብፅና ሶማሊያን በማሳያነት አንስተዋል።

ለዚህም የደህንነት ስጋቶችንና ሰብዓዊ እርዳታዎችን በምክንያትነት እንደሚያነሱ አስታውቀዋል፡፡

አሁን ያለው የአሜሪካ መንግስት አስተዳደርም እየሄደበት ያለው መንገድ በሌሎች ሀገራት ላይ ሲከተለው የነበረ ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ይህንኑ በኢትዮጵያ ላይ ለመድገም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

“ይህን ተግባሩን በኢትዮጵያ ላይ ለመፈፀም መንደርደሩ የሚያሳዝን ነው፣ የባይደን አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመምጣቱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ እንደሚፈልግ የሚያሳዩ ፍንጮች ነበሩ” ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ እንደማሳያ ማህበራዊ ሚዲያውን በተለይ ደግሞ ቲዊተር ላይ ኢትዮጵያን የተቃረኑ መረጃዎች ሲለቀቁ እንደነበር ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የውጭ ኃይል እንዲገባባት የማትፈልግና የማትፈቅድ ሀገር ናት ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ይህን ባለመረዳት የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታትም የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ያሳይ በነበረው አቋም ጥያቄ ስለነበረኝ በተለያዩ ጊዜያት ድምጼን አሰምቻለሁ ብለዋል፡፡

በተለይ የአሜሪካ መንግስት የወቅቱ አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ ውሳኔ ከማርቀቁ አስቀድሞ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ሳያወያይ እና በጉዳዩ ላይ ጥልቅ መረጃ ሳይኖረው በችኮላ ውሳኔ ለማሳለፍ መወሰኑ እንዳሳዘናቸው አመልክተዋል፡፡

በተለይ በኮንግረስ አባሏ ኬራን ባስ አማካኝነት የተረቀቀው ሪዞሉሺን 445 የተሰኘው ውሳኔ በጥልቅ ያልታየና ውስጡ ያልተፈተሸ የውሳኔ ረቂቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ የታቀደው ረቂቅ ውሳኔ መፍትሄ አመላካች እንዳልሆነ ያስታወቁት አቶ ቴዎድሮስ፣ የውሳኔ ሀሳብም ከአሜሪካ ኮንግረስ የማይጠበቅ ተግባር መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ይህ ውሳኔ “ባሳለፍነው ሳምንት ለሴኔቱ መቅረብ የነበረበት ጉዳይ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ባደረጉት ርብርብ አሁን ጉዳዩ እንዲቆም ሆኗል፣ ኮንግረሱም ዳግም እንደሚያጤነው ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።

“እናት ኢትዮጵያ ወልዳኝ አባት አሜሪካ አሳድጎኛል።እነዚህ ሁለት ዘመዳሞች በተሳተተ ጉዳይ እንዲጋጩና እንዲለያዩ አልፈልግም” ነው ያሉት።  

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚይዘው አቋም እውቀትና ሀብት እንዳለው አገር ሚዛናዊ መሆን ይጠበቅበታል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ለዚህም በግላቸው ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

“ይህን የማድረግም ኃላፊነት አለብኝ፤ በማለት ተሳስተው የኢኮኖሚም ሆነ ሌሎች እቀባዎች ቢያደርጉ” ህዝብ ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል አስቀድሞ ማሳወቅ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቅርቡ በኮንግረስ አባሏ ኬረን ባስ አማካኝነት የረቀቀው ውሳኔም ቢሆን ያለ በቂ ጥናት ለውሳኔ የቀረበ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ቴዎድሮስ፣ የኮንግረስ አባላቱ በችኮላ የተረቀቀ የውሳኔ ሀሳብ መሆኑን አውቀው በጉዳዩ ላይ ከመወሰን እንዲታቀቡ እየመከርን ነው ብለዋል፡፡

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን የጠቀሱት የቀድሞው የኮንግረስ እጩ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር በየትኛውም የሀገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ መሳተፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ ዓለማየሁ እ.ኤ.አ በ2018 የአሜሪካ ምርጫ የመጀመሪያው ትውልደ ኢትዮጵያዊ የአሜሪካ ኮንግረስ እጩ ሲሆኑ፤ የአሜሪካ ዶክተሮች ለአፍሪካ ማህበር መስራችና ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም