ቀጥታ፡

የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው ሰራዊት ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2013(ኢዜአ) የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዋዕትነት በመክፍል ላይ ለሚገኘው ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

ክልሉ በማንኛውም የመከላከያ እርክን ላይ የሚገኝ ሰራዊት ከማዕረጉ በተጨማሪ "ጀግና" ተብሎ እንዲጠራ በጨፌ መወሰኑ ይታወሳል።

የኦሮሞ አርቲስቶች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አጋርነታቸውን ያሳዩበት ዝግጅት በአዲስ አበባ ኦሮሞ ባሕል ማዕከል ተካሂዷል።

በመድረኩም የመከላከያ ሰራዊቱን ጀግንነት የሚዘክሩና ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ የሚያነሳሱ የኪነ-ጥብብ ስራዎች ቀርበዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጫልቱ ሳኒ፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እየተጋ የሚገኙት የሰራዊት አባላት ታሪክ የማይዘነጋቸው ጀግና የኢትዮጵያ ባለውለታዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ለሰራዊቱ እውቅና ለመስጠትና ጀግንነቱ ለትውልድ እንዲተላለፍም የክልሉ መንግስት የሰራዊቱ አባላት "ጀግና" ተብለው እንዲጠሩ በጨፌው መወሰኑን አስታውሰዋል።

ሰራዊቱ ለዚህች ሀገር የከፈለው መስዋዕትነት ለታሪክ የሚተላለፍ ነው ያሉት ወይዘሮ ጫልቱ፤ ጀግንነታችሁንም ታሪክ ያወሳዋል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት በሁሉም ዘርፍ ለሰራዊቱ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በቀጣይም አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

በዛሬው ዕለት የተሰናዳው የኪነ ጥበብ መድረክም የክልሉ ህዝብና መንግስት ከሰራዊቱ ጎን መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ብልጽግና የምናረጋግጥበት ጊዜ እሩቅ አይደለም ያሉት ወይዘሮ ጫልቱ፤ የፊታችን ብሩህ እንዲሆንም ሁሉም የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከመከላከያ ሚኒስቴር የተወከሉት ጀነራል ቡልቲ ታደሠ በበኩላቸው፤ የኪነ ጥበብ ስራዎች ሰራዊቱ ሞራል እንዲያገኝና የቆመለትን ዓላማ በድል እንዲያጠናቅቅ ስንቅ ይሆነዋል ብለዋል።

ኪነ ጥበብ ከጥንት ጀምሮ የሰራዊቱ የሞራል አቅም መሆኑን አንስተው ለቀጣይም አርቲስቱ በኪነ ጥበቡ ከሰራዊቱ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ብዙነሽ መሠረት፤ የኦሮሚያ ክልል ለሰራዊቱ ድጋፍ ጥሪ ቀድሞ ምላሽ በመስጠቱ አመስግነዋል።

ኦሮሚያ ክልል ስንቅ አዘጋጅቶ በመላክ፣ የገንዝብ ድጋፍ በማድረግና የራሱን የጸጥታ ሃይልም በመላክ ግንባር ቀደም መሆኑን አንስተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰራዊቱ አባላት በሰጡት አስተያየትም ይህ ዓይነት ድጋፍ ሰራዊቱ እንዲነሳሳ ለማድረግ ከፍተኛ አቅም ይኖረዋል ብለዋል።

እነሱም ለቆሙለት ዓላማ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለሀገራቸው ዋጋ የሚከፍሉ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በኦሮሞ ባህል ማዕከል በተካሄደው መድረክ ላይ ከከልሉና ከፌዴራል የተለያዩ የመንግስት ሃላፊዎችና የሰራዊት አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም