ቀጥታ፡

በአንድነት ስንቆም ችግሮቻችንን በቀላሉ መፍታት እንችላለን---አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

ሐረር፤ ሐምሌ 27 ቀን  2013 (ኢዜአ) “በአንድነት ስንቆም ችግሮቻችንን በቀላሉ መፍታት እንችላለን” ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  ታገሰ ጫፎ ተናገሩ። 

አፈ ጉባዔው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ከሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ጋር በመሆን በሐረሪ ክልል  የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ጥገና  ስራን አስጀምረዋል።

አፈ ጉባኤ ታገሰ በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች በአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላና የአቅመ ደካሞችን ሕይወት ለመቀየር የቤቶች ጥገና መርሃ ግብር መጀመሩን አስታውቀዋል።

ሕዝቡን የልማቱ አካል አድርገን በአንድነት ከቆምን ችግሮቻችንን መፍታት እንደሚቻል መርሃ ግብሩ ያሳያል ብለዋል።

መንግሥት የአቅመ ደካሞችን ችግሮች ለማቃለልና የተረጋጋ ህይወት እንዲኖሩ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡም በዚህ ላይ  የነቃ ተሳትፎ  እንዲያደርግ አሳስበዋል። 

ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በጽናት መቆም ከውስጥም ከውጭ የሚቃጡብንን ጥቃቶች በጋራ መመከት እንደሚገባም አፈ ጉባዔ ታገሰ አስገንዝበዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፤ አቅመ ደካሞችን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች ማከናወን ኢትዮጵያዊነታችንን ስለሚያጎለብቱ መጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል።

ምክር ቤቱና ተጠሪ ተቋማት በክልሉ ያስጀመሯቸው ሥራዎች ብልጽግናን የሚያረጋግጡና የእርስ በርስ መረዳዳት ባህልን ስለሚያጎለብቱ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ  አቶ ተፈራ በቀለ በሰጡት አስተያየት፤ ምክር ቤቱና ተጠሪ ተቋማት የበጎ አድራጎት ሥራውን የመቻቻልና የመተሳሰብ ከተማ በሆነችው ሐረር ላይ መከናወኑ በሕዝቡ ዘንድ መነቃቃትን እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

ተቋማት  በበጎ አድራጎት ተግባራት መሳተፋቸው ለዜጎች ምሳሌ ከመሆን ባለፈ ሀገርን የሚገነባባቸውን መንገዶች ያመላክታሉ ብለዋል።

የበጎ አድራጎት ሥራ ማከናወን ዜጎችን ከመጥቀም ባለፈ ለራስም ቢሆን ደስታን የሚሰጥ ተግባር ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የስልጠናና ጥናት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አቤል አዳሙ ናቸው።

በተለይ በክልሉ ከተማና ገጠር ቀበሌዎች የሚካሄደው የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችን ጥገና ለሌላው ህብረተሰብ ማሳያና ማስተማሪያ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

የቤት ጥገና ስራ ከሚከናወንላቸው መካከል ወይዘሮ አበበች ገብሬ ሕዝቡና መንግሥት ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም