በድሬዳዋ አስተዳደር የኮሮናን ተፅዕኖን በመቋቋም አበረታች ስራዎች መከናወናቸው ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አስተዳደር የኮሮናን ተፅዕኖን በመቋቋም አበረታች ስራዎች መከናወናቸው ተመለከተ
ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 27/2013(ኢዜአ)በድሬዳዋ አስተዳደር በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የኮሮናን ተፅዕኖን በመቋቋም የተከናወኑት ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ሥራዎች አበረታች መሆናቸው ተመለከተ።
የአስተዳደሩ ምክር ቤት ሁለተኛ የሥራ ዘመን 47ኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡
የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ለጉባዔው ባቀረቡት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንዳሰረዱት፤ በዘመኑ ወረርሽኙን በመከላከል የተከናወኑ የልማት ተግባራት መልካም አፈጻጸም ተመዘግቦባቸዋል፡፡
በምጣኔ ሃብቱ ዘርፍ 1ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ከግብር ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 87 በመቶ መሳካቱን ጠቅሰዋል፡፡
ይህም የአስተዳደሩን ነዋሪዎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ አቅም እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ከታቀዱ ፕሮጀክቶች 84ቱ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አቶ አህመድ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የከተማውን የሥራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ ለ23 ሺህ ሰዎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 16 ሺህ የሚጠጉ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል፡፡
በዚህም ወጣቶችና ሴቶችን በምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ያላቸውን ተጠቃሚነት ማሳደጉን አመላክተዋል ፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የ102 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩንም ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል፡፡
ድሬዳዋን የምሥራቅ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ በተከናወኑ ሥራዎች 25 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡
ባለሃብቶች በግንባታና ስራ በሚጀምሩበት ወቅት ለ23 ሺህ ሰዎች ቋሚና ለ11 ሺህ 500 ሰዎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡
በገጠር ልማት በኩልም የተከናወኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የውሃ አቅርቦትን ከ70 ወደ 80 በመቶ ማሳደጋቸውን አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም 320 ሄክታር መሬት የሚያለሙ የአነስተኛ መስኖ አውታሮች በመገንባት 147 ቤተሰቦች በቤተሰብ ደረጃ በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ መሰራቱም ተጠቅሷል፡፡
እንደ ምክትል ከንቲባ ማብራሪያ ፤በጤናው ዘርፍ ኤች አይ ቪ ቫይረስ ከእርጉዝ ሴቶች ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ መከላከል ተችሏል፤ የእናቶችና የህጻናት ሞትን በመቀነስ ጥሩ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡
የትምህርትን ተደራሽነት በማስፋት 102 የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል፡፡
ምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና የምክር ቤቱ አባላት ከፕሮጀክቶች መጓተትና ከመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ጋር ለሚነሱ ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡
ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን መከላከልና ህገ-ወጥ ግንባታን ለማስቀረት መስራት እንደሚያስፈልግም እንዲሁ፡፡
ምክር ቤቱ በሪፖርቱ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል፡፡
ጉባኤው በ2014 በጀት ዓመት መሪ እቅድና ለምክር ቤቱ ተጠሪ በሆኑ ተቋማት ሪፖርቶች ላይ እንደሚወያይ የሚጠበቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ከድሬዳዋ ዘግቧል፡፡