የደቡብ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጉባኤ ለዳኞች ሹመት በመስጠትና አዋጆችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጉባኤ ለዳኞች ሹመት በመስጠትና አዋጆችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ
ሃዋሳ ፤ ሐምሌ 27/2013 (ኢዜአ) የደቡብ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ስድስተኛ የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ለ146 ዳኞች ሹመት በመስጠትና የተለያዩ አዋጆችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ።
ምክር ቤቱ በዛሬ የሁለተኛ ቀን ውሎው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋናው ኦዲት መሥሪያ ቤት ሪፖርቶችንም አድምጧል።
ዛሬ ሹመት ከተሰጣቸው 146 ዕጩ ዳኞች መካከል 22 ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆኑ፤ 124 ለወረዳና ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የተሾሙ ናቸው።
የዳኞቹን ሹመት ለምክር ቤት ያቀረቡት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አጎ ተሿሚዎቹ ባላቸው የትምህርት ደረጃ፣ አገልግሎትና መልካም ስነምግባር መመረጣቸውን አስረድተዋል።
በተጨማሪም በሚመለከታቸው አካላት ለቦታው የሚመጥኑ መሆናቸው መረጋገጡን ነው የገለጹት።
ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው ካጸደቃቸው አዋጆች የጌዴኦ ባህላዊ መልከኣ ምድር ቅርሶችን ለመጠበቅ የወጣው ረቂቅ አዋጅ አንዱ ነው።
የማህበረሰብን ተፈጥሮአዊ የአካባቢ ጥበቃ ስርዓት ለማጠናከር አዋጁ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይለማሪያም ተስፋዬ አብራርተዋል።
"በቀጣይም የማህበረሰቡን ባህል በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ሥራዎች ትኩረት ይሰጣቸዋል" ብለዋል።
የክልሉ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያና የዋናው ኦዲት መሥሪያ ቤት አዋጅን ለማሻሻል የወጡ ረቂቅ አዋጆችም ዛሬ በምክር ቤቱ የጸደቀ ሌላው ነው።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አጎ እንዳሉት፤ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ ለንቃተ ህግ ማጎልበት ሥራ ትኩረት ተሰጥቷል።
አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግና ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓትን ለማጠናከር መሠራቱንም አመልክተዋል።
በበጀት ዓመቱ በፍትሀ ብሔርና ወንጀል ጉዳዮች ከቀረቡ 214ሺህ 152 መዝገቦች ለ195ሺህ 298 እንዲሁም
ለሰበር ሰሚ ችሎት ከቀረቡ 3ሺህ 234 መዝገቦች ለ2ሺህ 886 ውሳኔ መሰጠቱንም ጠቅሰዋል።
ምክር ቤቱ በበኩሉ የመንግስት ሀብት ምዝበራ፤ የሴቶች ጥቃትና የግድያ ወንጀሎችን ለመከላከል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተገቢና አስተማሪ እርምጃዎችን እንዲያጠናክር አሳስቧል።
የክልሉ ዋና ኦዲተር ወይዘሮ ፈዲላ አደም የኦዲት ግኝትን ለምክር ቤቱ አባላት በዝርዝር አቅርበዋል።
የፋይናንስ አስተዳደርና አሰራር ላይ የተስተዋለው ችግር ለሀብት ብክነት ያለውን ድርሻ በመግለፅ ለማስተካከል የምክር ቤቱን ድጋፍ ጠይቀዋል።
ምክር ቤቱ ትናንትና ዛሬ ያካሄደው ጉባኤ የሥራ ዘመኑ ማጠቃለያ መሆኑን የዘገበው በስፍራው የሚገኘው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ነው።