ቀጥታ፡

በሀገር ሉዓላዊነት የማይደራደሩ ክንዶች

መንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)

"ሀገሬን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እቆማለሁ!!"

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ከውስጥና ከውጭ ከባድ ፈተናዎች እንዳጋጠሟት የታሪክ ድርሳናት የሚያወሱት ሲሆን በሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ተደራድረው እንደማያውቁ መላው ዓለም የመሰከረለት እውነታ ነው። በተለየ መልኩ የሚታወሰው የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያንን በአንድነት አሰባስቦ ለታላቅ ድል ማብቃቱ በዓለም የታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ በተለያየ ጊዜያት ተመስክሮለታል። 

ከባለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የዘር ከፋፋይነት ፖለቲካ ያከተመበትና የለውጥ ተስፋ የታየበት በአንፃሩ ደግሞ ከውስጥም ከውጭም ፈተናዎች የተጋረጡበት ሁኔታ ታይቷል። የእነዚህ ፈተናዎች ዋነኛ መንስኤ የሆነው የህወሓት ቡድን ሲሆን በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ በመቃወም ወደ መቀሌ መሽጎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በዘረጋቸው መረብ አማካኘነት ሀገር ለማፍረስ ሲሰራ ቆይቷል።        

የህወሓት ቡድን ሀገር የማተራመስ ህልሙን ለማሳካት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም  በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ በሌሊት ጥቃት በመፈጸም ክህደቱን አሳይቷል። ይህን ጥቃት ከመፈጸሙ አንድ ቀን አስቀድሞ የቡድኑ ግንባር ቀደም መሪ የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጦርነት የማይቀር ስለመሆኑና የትግራይ ህዝብ ለዚህ  እንዲዘጋጅ በወቅቱ በነበረው የትግራይ መገናኛ ብዙሃን በኩል በይፋ አሳውቀው እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚሁ ንግግራቸው “ወደ ትግራይ የሚመጡ ማናቸውም አካላት እንቀብራቸዋለን” የሚል ቅስቀሳም አድርገዋል።

የኢትዮጵያውያንን የለውጥ ፍላጎት ለመግታት ብቻ ሳይሆን ሀገር ለማፍረስ ታጥቆ የተነሳውን የህወሓት ቡድን ለህግ ለማቅረብ መንግስት በወሰደው አፋጣኝ ህግ የማስከበር እርምጃ ቡድኑ ተንኮታኩቷል፤ የወጠነውም ሀሳብ ከንቱ ሆኖበታል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት እንዳይፈጠር ዓላማ ያነገቡ ከቡድኑ ጋር የቆየ ትስስር ያላቸው የውጭ ሃይሎች ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ ከፍተኛ ዘመቻ ከፍተዋል። እነዚህ የውጭ ሃይሎች በሰብአዊ መብት ሽፋን የኢትዮጵያን ገጽታ ለማበላሸት በሁሉም አቅጣጫ ተቀናጅተው ሲሰሩ ቆይተዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል ከነበረው ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ በተጨማሪ በአንድ በኩል በህዳሴው ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በሌላ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደውን ምርጫ የተሳካ ለማድረግ  ግብ ይዞ ሲሰራ በነበረበት ሁኔታ ምእራባውያን ሀገራት ከፍተኛ ተጽእኖ ለማሳደር ጥረት አድርገዋል።

የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት እንዳይከናወን ምርጫውም እንዳይካሄድ መመሪያ እስከመስጠትም ደርሰው ነበር። ይሁን እንጂ ህዝቡ ባሳየው አንድነት እና ቆራጥነት ምርጫው በስኬት ሲጠናቀቅ የግድቡ ሙሌትም በታቀደው መሰረት በመፈጸሙ ውጥናቸው ሊሳካ አልቻለም።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ለህብረተሰቡ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ “በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ብዙ አይተናል፣ ብዙ ተፈትነንበታል። በራሳችን ዓቅም መቆማችን የሚያስደነግጣቸው፣ በፍላጎታችን መመራት መጀመራችን የሚቆጫቸው ብዙ ጋሬጣዎችን ሲጥሉብን ነበር” በማለት በኢትዮጵያ ላይ ምን ያህል ጫና እንደነበር ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን ጫናዎችንና ፈተናዎችን እንዴት ተቋቁመው እንደተሻገሩና አንድነታቸውን እንዳጠናከሩ ሲገልጹም “ሚስማር አናቱን ሲመቱት ይበልጥ ይጠብቃል” በማለት ነበር የገለጹት።

በትግራይ ክልል የተካሄደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተከትሎ ምእራባውያን ሀገራት በሰብአዊ መብት ሽፋን መንግስትን ለማንበርከክ የሪፖርት እና የመግለጫ ጋጋታዎችን በማድረግ ጫና ለማሳደር ጥረዋል። መገናኛ ብዙሃኖቻቸው እና የህወሓት ተከፋይ አክቲቪስቶችም ፕሮፖጋንዳዎችን ጭምር በማሰራጨት የኢትዮጵያውንን የሞራል ስብእና ለማዳከም ሰርተዋል፤ አሁንም እየሰሩ የገኛሉ።

ምእራባውያን በተለይ አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ከህወሓት ጋር ድርድር እንዲደረግ፣ የወሰን ጉዳዮችን በማንሳት “ምንም መንካት” አትችሉም በሚል ትእዛዝ ሲሰጡ ከርመዋል።  

በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ߵሩሲያ በውስጥ ጉዳዬ ላይ ጣልቃ ልትገባ ነው ይህ ደግሞ ግልጽ ሉዓላዊነትን መጋፋት ነውߴ በማለት ሩሲያን ከሰዋል። ይሁን እንጂ አሜሪካ በሌሎች አገሮች ጣልቃ በመግባት ስለምትፈጽመው ጉዳይ ጥፋት መስሎ አይታያትም።  ይህ የፕሬዚደንቱ ንግግር በሉዓላዊ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ወንጀል የሚሆነው በአሜሪካ ላይ ሲፈጸም ብቻ ነው ወይ የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሴ ይህን በተመለከተ ሲገልጹ ߵአሜሪካ አንድን ጉዳይ ለመፈጸም እና ላለመፈጸም ከራሷ ብሔራዊ ጥቅም ጋር ብቻ በማነጻጸር እንጂ ከሌሎች ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም ጋር አታነጻጽረውምߴ ብለዋል።

አሜሪካ ለህግ እና ለሞራል ቦታ እንደሌላት የሚገልጹት ምሁሩ አሜሪካ ለመሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች የምትጨነቅ ቢሆን ኖሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መተዳደሪያ ህግ ላይ የሰፈረውን ለሀገራት በውስጥ ጉዳያቸው የመወሰን ሙሉ መብት የሚሰጠውን የሉዓላዊነት መብት ታከብር እንደነበር አክለው ገልጸዋል።  

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ዶክተር ደመቀ አጪሶ በበኩላቸው የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን የዕርዳታ እህል ወደ ትግራይ እንዳይገባ ሲከለክል፣ ህጻናትን ለጦርነት ሲያሰልፍ በግልጽ እየተመለከቱ ዝምታን መምረጣቸው ለሰብአዊ መብት ደንታ እንደማይሰጡ ማሳያ ነው በማለት ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያን መንካት አፍሪካን መንካት ነው”  የሚሉት የሰላም እና ደህንነት ተመራማሪው ዶክተር ዮናስ አዳዬ ߵየአሜሪካን የውጭ ግንኙነት እንመርምር ከተባለ በየትኛውም አካባቢ ጠንካራ መንግስት እንዲወጣ አይፈልጉም፡፡ ከወጣም እነሱ በሚፈልጉት መንገድ መጓዝ አለበት ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

ከአሜሪካ ቁጥጥር ውጭ በመውጣት በራሱ ሳንባ የሚተነፍስ ከሆነ ብሄራዊ ጥቅማቸውን የሚጻረር አድርገው ይወስዱታል ይላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ቀደም ሲል የነበረውን የውክልና መንግስት ካልተመለሰ ብሔራዊ ጥቅማችንን በአፍሪካ ማስጠበቅ አንችልም የሚል ስጋት የገባቸው በማለትም ያክላሉ፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ በመወሰን መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል እንዲወጣ ማድረጉን እንደሽንፈት በመውሰድ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዘውን እኩይ ዓላማ ለማሳካት በተለያዩ ቦታዎች ጦርነት በመክፈት ትንኮሳ ጀምሯል።

ምእራባውያንም የመንግስትን የተኩስ አቁም ውሳኔ ከማድነቅና በአሸባሪው ሃይል ላይ ጫና ከማሳደር ይልቅ ዳግም ተመልሶ ስልጣን እንዲቆናጠጥ በማሰብ የሚፈጽማቸውን ትንኮሳዎች በዝምታ አልፈውታል። ይልቁንም  በኢትዮጵያ ላይ ጫናው ከምንጊዜውም ይልቅ ለማክበድ እየሰሩ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የውስጥና የውጭ ጫናው በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም ይልቅ አንድ ላይ እንዲቆሙ አድርጓቸዋል። 

  "ሀገሬን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እቆማለሁ!!" በማለት ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነቃንቋል። ይህ ንቅናቄ ኢትዮጵያውያን የሀገር ሉአላዊነትን በማስቀደም ለጠላት የማይንበረከኩ መሆናቸውን ለዓለም አሳይቷል። ይህ የህዝብ ንቅናቄ አንዳንድ የአሜሪካ ሴናተሮችን አቋም እንዲቀየር አስችሏል። ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ የመቆም እና ሉዓላዊነትን የማስከበር የቆየ እሴቶቻችንን  በማስቀጠል ዓለምን አስደምመናል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም