ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ፀንታ እንድትቆም የሠላም ተምሣሌት የሆኑት የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን ጥበብ ሊጠቀሙ ይገባል

ሀምሌ 27/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ፀንታ እንድትቆም የሠላምና አንድነት ተምሳሌት የሆኑ የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን ጥበብ መጠቀም እንዳለባቸው የሠላም ሚንስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ 13ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ዛሬ አካሂዷል።

በጉባዔው የሠላም ሚኒስትሯን ጨምሮ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የጉባዔው የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ጉባዔው ሠላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና መከባበርን በሃይማኖታዊ መንገድ ለመገንባት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት የተስተዋሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች በሠላም እንዲፈቱ ጉባዔው ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ጥረት ሲያደርግ እንደነበረም አስታውሰዋል።

የአገር ሠላም በምኞትና ፍላጎት ሳይሆን የሰዎችን አስተሳሰብ አዎንታዊ ለማድረግ በሚደረግ ጥረት የሚመጣ በመሆኑ የሃይማኖት አባቶች የሠላም ሐዋርያ ለመሆን በትጋት ልንሰራ ይገባልም ብለዋል።

የጉባዔው ዋና ፀሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለም ጉባዔው በቀጣይም ግጭቶች በውይይትና በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

በትግራይ ክልል ያለው ችግር በሕዝብ መካከል ያለመሆኑን ገልፀው ጉባዔው የሕዝብ ለሕዝብ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ጉባዔው ላለፉት ዓመታት አገራዊ ፋይዳና ትርጉም ባላቸው ጉዳዮች ላይ በንቃት ሲሳተፍ መቆየቱን ገልጸዋል።

አገሪቷ ችግር በገጠማት ጊዜም ምዕመናን በመንፈስ ጠንክረውና ፀንተው እንዲቆሙ ፆም፣ ፀሎትና ምህላ በማወጅ መንፈሳዊ ጥንካሬን በማላበስ ያደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና የሚቸረው መሆኑንም አክለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ቋንቋችን ሠላም፣ አንድነት፣ አብሮነትና ፍቅር ካልሆነ ፖለቲካ ብቻውን አገር የማፅናት አቅም የለውም ያሉት ሚኒስትሯ የሃይማኖት አባቶች በመከራ ጊዜም የወትሮው አባትነታቸው መታየት አለበት ብለዋል።

የተጋረጠብንን አደጋ በጋራ ለመመከት የምንችልበት መንፈሳዊ ስንቅና ፅናት ያስፈልገናል ነው ያሉት።

የሕልውና ዘመቻው በውዴታ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ስለሆነ የተገባበት መሆኑንና ይህን ፈተና በጋራ ፀንቶ ማለፍም የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የሠላምና የአንድነት ተምሳሌት የሆኑት አባቶች በምህላና ፀሎት ምዕመናንና ኢትዮጵያ ፀንተው እንዲቆሙ ያላቸውን ጥበብ መጠቀም እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በአገር ጉዳይ ቀደምት አባቶች የከፈሉትን አይነት መስዋዕትነት መክፈል ጭምር እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት።

ያጋጠመው ቀውስ በአንድ እናት ልጆች እየተደረገ ያለ መሆኑ ውስብስብና ፅናት የሚጠይቅ እንዳደረገው አንስተው የኢትዮጵያን ዘላቂ የሠላም፣ የልማትና የብልፅግና ጉዞ ማስቀጠልን መንግስት ለአፍታም የማይዘነጋው መሆኑን አረጋግጠዋል።

ጉባዔውን ለማገዝ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም