ቀጥታ፡

የደቡብ ክልል ህዝቦች ለህልውና ዘመቻው ስኬታማነት ድጋፋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል ህዝቦች የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ለህግ አስከባሪው ኃይል ያላቸውን አጋርነት ለማረጋገጥ ድጋፋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። 

የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የክልሉ ህዝቦች እኛ እያለን ሃገራችን ለብተና አትዳረግም በሚል ቁጭት ተነሳስቷል።

በዚህም ለህግ አስከባሪው ኃይል ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን በተግባር ለማረጋገጥ  እየተንቀሳቀሱ  መሆናቸው ተመልክቷል።

ህዝቡ የሚያደርገው ድጋፍ ለተገቢው ዓላማ እንዲውል ለማድረግ ኮሚቴ መቋቋሙንና በዚህም ከ250 ሚሊየን ብር በላይ በዓይነትና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ በየደረጃው ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ከታቀደው ውስጥም  በመጀመሪያው ዙር የተሰበሰበ 37 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ባለፈው ሳምንት ለመከላከያ ሚኒስቴር ማስረከባቸውን አውስተው፤ ቀጣዩ ዙር ደግሞ በመጪው ሃሙስ ለማስረከብ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

በድጋፉ ሂደት የሴቶችና የወጣቶች የተደራጀ ተሳትፎ ጉልህ መሆኑን ያመለከቱት ሃላፊዋ፤ መላው የክልሉ ህዝብ ላደረገው የድጋፍና ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚህ በፊት አሸባሪው የተለያዩ የውስጥና የውጭ ሃይሎችን በመጠቀም በክልሉ አለመግባበቶችን በመምራት ህዝቡ ተቻችሎ የሚኖርበትን ብዝሃነት ለግጭት ሲጠቀም መቆየቱንም አስታውሰዋል።

የክልሉ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ከህዝቡ ጋር በመተባበር ይህንን ሴራ በማክሸፍ ሃላፊነቱን በመወጣት አሁን ደግሞ በሃገር ህልውና ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት ልዩ ሃይሉ በሁለት ዙር ግንባር መዝመቱን ተናግረዋል።

የሃገር ጥሪውን ተከትሎ ሰራዊቱን ለመቀላቀል የወሰኑ ከ5 ሺህ 500 በላይ የክልሉ ወጣቶች ወደ ማሰልጠኛ መግባታቸውን ጠቅሰው የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ  የክልሉ ህዝቦችና መንግስት ደጋፍ   ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የጥፋት ሃይሉ ሃሰተኛ መረጃዎችን በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ማሰራጨትን እንደ አማራጭ ተጠቅሞ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ህብረተሰቡ የሚሰማው መረጃ ከትክክለኛ ምንጭ  በማረጋገጥ ለህልውና ዘመቻው ስኬታማነት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም