ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮና ተጠሪ ተቋማት ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ደም ለገሱ

ሐምሌ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮና ተጠሪ ተቋማት ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ደም ለገሱ።

የተቋማቱ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተቋም አመራሮችና ሠራተኞች እንዳሉት፤ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ያሳዩትን አንድነት በህልውና ዘመቻውም ይደግሙታል።

አንድነትን በማጠናከር የአሸባሪው ህወሃትን ለመዋጋት በአንድነት ስሜት እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል።

የቢሮውና የተጠሪ ተቋማቱ ሃላፊዎችና ሠራተኞች "ደማችን ለመከላከያ ሠራዊታችን" በማለት ደም ለግሰዋል።

"ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን የውስጥና የውጭ ችግሮች ለማሸነፍ የሚቻለው ሕዝብ አገሩን ሲያስቀድም ነው" ብለዋል።

"የጦርነትን አስከፊነት የማይረዳ የለም" ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ አሸባሪው ህወሃት እየፈጸመ ያለው ጥቃት የአገር ክህደት መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ህወሓት የሚፈጽመውን ጥቃት ተከትሎ እየታየ ያለው የውጭ ጫናና ጣልቃ ገብነት አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል።

ይህንን ጫና መቋቋም የሚቻለው አገራዊ አንድነትን በማጠናከር እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የሕልውና ዘመቻውን ለማደናቀፍና አገር ለማሸበር የሚጥሩ ሰርጎ ገቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ ሁሉም ዜጋ ለአካባቢው ሠላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

አገር ከገጠሟት የውስጥና የውጭ ሃይሎች ነፃ እስከምትወጣ ድረስ ከመከላከያ ሠራዊቱና ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ያረጋገጡት አስተያየት ሰጪዎቹ ሁሉም ዜጋ ይህንኑ እንዲያደርግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም