ቀጥታ፡

ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብሮ ሀገር ለማፍረስ እየተፍጨረጨረ ያለውን ከሀዲ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ይገባል- ምሁራን

ደሴ፤ ሀምሌ 27/2013 (ኢዜአ) ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብሮ ሀገር ለማፍረስ በሙሉ አቅሙ እየተፍጨረጨረ ያለውን ከሀዲው የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ይገባል ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ቡድኑ የኢትዮጵያን አንድነት በሚፈልጉ የትግራይ ተወላጆች ላይ ሳይቀር ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን ምሁራኑ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አልዩ ውዱ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት  ቃለ ምልልስ እንደገለጹት አሸባሪው ቡድን ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በስልጣን በቆየባቸው አመታት  በኢትዮጰያዊያን ላይ አሰቃቂ ግፍና በደል ፈጽሟል።

ቡድኑ የፖለቲካ ስህተቱንና የሚፈጽማቸውን ግፍና በደሎች ተገቢ አለመሆናቸውን የሚተችን ሰው በአሸባሪነት እየፈረጀ ሲፈጽም የነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከኢትዮጵያ ህዝብ አዕምሮ መቼም የሚጠፋ አለመሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ቡድን ከዚህ ቀደም የፈጸመው በደልና ግፍ አልበቃ ብሎት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት ላይ ከጀርባ ጥቃት በመፈጸም በታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ  የማይታወቅ የሀገር ክህደት መፈጸሙን አስታውሰዋል ።

ቡድኑ አሁን ላይ ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ወግኖ ሀገር ለማፍረስ በሙሉ አቅሙን እየተፍጨረጨረ በመሆኑ በኢትዮጰያዊያን የተባበረ ክንድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊወገድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"ቡድኑ ሀገር ለማፍረስ በከፈተው ጦርነት  ጨቅላ ህጻናትን በማሰለፍ እንዲሁም  ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ በማስተጓጎልና መሰረተ ልማት በማውደም ለትግራይ ህዝብ ጭምር ታሪካዊ ጠላት መሆኑን በተግባር አሳይቷል" ብለዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ ተረጋግቶ በማሰብና ከሀዲው ቡድን እንደማይጠቅመው በመገንዘብ ከሌሎች ኢትጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስወግደው እንደሚገባ ዶክተር አልዩ አመልክተዋል።

የህወሓት ቡድን ከምስረታው ጀምሮ  የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ እርስ በእርስ በማጫረስ የእኩይ ሴራውን መተግበር መጀመሩን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ፖለቲካ ሳይንስ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ይመር አሊ ናቸው።

"ቡድኑ በተለይም በስልጣን በቆየባቸው 27 ዓመታት ሀገር ወዳድ ምሁራንን፣ ፖለቲከኞችን፣ ወጣቶችንና የኢትዮጵያን እደገትና አንድነት የሚሹ ዜጎችን ሁሉ እያሳደደ በአሰቃቂ ሁኔታ ከመግደሉ ባለፈ አኮላሽቷል፤ አካለ ጎደሎም አድርጓል" ብለዋል፡፡

"የኢትዮጵያን አንድነትና እድገት የሚፈልጉ የትግራይ ተወላጆችንም እንደሌሎች ብሔሮች ሁሉ በመጨፍጨፍ እንዲሰደዱ አድርጓል" ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አሁንም የራሱን እድሜ ለማራዘም መሳሪያ መሸከም የማይችሉ ህጻናትን ወደ እሳት እየማገደ ነው " ሲሉም አመልክተዋል።

"የኢትዮጵያ ጠላትና ነቀርሳ የሆነውን ከሀዲውን ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስና ለማሶገድ  ሁሉም ኢትዮጵያዊ  አንድነቱን ጠብቆ ሊነሳ ይገባል" ብለዋል።

ህዝቡ ቡድኑን በማስወገድ የሀገርን ህልውና ለማስከበር እየተፋለመ ካለው መከላከያ ስራዊትንና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጎን በመቆም ድጋፉን ማጠናከር እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

"ህዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ መንግስት ያቀረበውን  ጥሪ  በመቀበል የሰጠው ፈጣን ምለሽ አደዋን ከማስታወሱም ባለፈ የህልውና ዘመቻው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ  እድል ይሰጣል" ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ህዝባዊ ንቅናቄው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።

"በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ህወሓት አይነት የውስጥ ጠላት፣ ባንዳና ሀገር አፍራሽ ቡድን ገጥሞን አያውቅም" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ምስጋናው ታደሰ ናቸው፡፡

"ሁሉም ዜጋ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ አሸባሪውን ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ሊያሶግድ ይገባል" ብለዋል፡፡

ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ አሸባሪውን ቡድን በማውገዝና መከላከያ ስራዊቱን በመደገፍ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ዶክተር ምስጋናው አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም