ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የህወሃት የሽብር ቡድን በጋራ ለመዋጋት ዝግጁ ነን- የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የህወሃት የሽብር ቡድን በጋራ ለመዋጋት ዝግጁ ነን- የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፣ሐምሌ27/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የህወሃት የሽብር ቡድን በጋራ ለመዋጋት ዝግጁ ነን ሲሉ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።
''ለአገራችን ሰላምና ሉዓላዊነት መጠበቅ በቁርጠኝነት እንታገላለን'' በሚል መርህ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ህዳሴ ፓርቲ፣ ራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲና የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ ናቸው በጋራ መግለጫ የሰጡት።
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የህወሃት የሽብር ቡድን ለመዋጋት ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
መንግስት ያደረገውን ጥሪ በመቀበል ለአገራቸው ህልውና በመሰለፍ አሸባሪውን የህወሃት ቡድን እስከመጨረሻው ለማጥፋት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የፓርቲዎቹ አባሎችም ይሁኑ አመራሮች እስክ ግንባር በመዝመት የአገር መከላከያ ሰራዊትን ለማገዝና አሸባሪውን ለመዋጋት ዝግጁ እንደሆኑም ነው የተናገሩት።
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሰና የሕዳሴ ፓርቲ ዋና ጸሓፊ ኢንጀነር ሱራፌል እሸቱ ጠንካራ አንድነት ያለውን ሕዝብ የደፈረ ቡድን ከመደምሰስ እንደማይተርፍ ይናገራሉ።
በማንኛውም ሁኔታ የትግራይንም ህዝብ ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዚህ አሸባሪ ቡደን ለማላቀቅ ለመታገል ተዘጋጅተናል ብለዋል ፓርቲዎቹ።
የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው አማረና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርተ ፕሬዚዳንት አቶ ዘርይሁን ገብረእግዚያብሔርም ''ኢትዮጵያ በምትፈልገን ቦታ ሁሉ ለመሰለፍ ዝግጁ ነን'' ብለዋል።
አሽባሪውን የህወሃት ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው አገራዊ ትብብር ጠንካራ ተሳትፎ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።
የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ከበደ ደግሞ አሸባሪውን ማጥፋት ለከፍተኛ ችግር የተዳረገውን በተለይ የትግራይ ሕዝብ ማዳን ነው ብለዋል።
ለዚህ በጎ ተግባር ሁሉም አገር ወዳድ ዜጎች እንዲሁም የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራርና አባላት እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።