ኢትዮጵያውያን የአሸባሪውን ግፍና በደል እስከ መቼ ይታገሱ?

33

ሐምሌ 27/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማድረግ ላለፉት 16 ዓመታት ጉልህ አስተዋፅኦ ያላቸው ኢንጅነር ጌታነህ ባልቻ አሁን ላይ የባልደራስ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ናቸው።

ከዚህ ቀደም አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከአባልነት እስከ አመራርነት ተሳትፎ አድርገዋል።

ኢንጅነር ጌታነህ በወያኔ የበላይነት ይመራ በነበረው የአገዛዝ ዘመን በፖለቲካ ተሳትፏቸው ብዙ ግፍና መከራ እንደደረሰባቸው ይናገራሉ።

እርሳቸውን ጨምሮ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ያደርጉ የነበሩ በርካታ ግለሰቦች ላይ ህወሃት የተለያዩ በደሎችን ማድረሱንም ያስታውሳሉ።

የህወሃት የሽብር ቡድን በተለይም ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ የበሰለ የፖለቲካ ሃሳብ ያላቸውን የፓርቲ አመራሮችና አባሎች አሳድዶ በማሰር፣ በማሰቃየትና በመግደል ጭምር ከባድ ወንጀል ፈፅሟል ይላሉ።

በጊዜው ኢንጅነር ጌታነህን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ስቃይ እየገጠማቸውም የህወሃትን የግፍና የጭቆና አገዛዝ በመቃወም መታገላቸውን ያስታውሳሉ።

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት እንዲሁም ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶች በህወሃት የማይታሰቡ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ቡድኑ ገና ወደ ስልጣን ሲመጣ ጀምሮ ሰብዓዊ መብቶችን መጣስና ማፈን የለመደውና የተካነበት ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።

እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ የትግል አጋሮቻቸው የአሸባሪ ቡድኑን ድርጊት በመቃወማቸው ብቻ ከእስር ጀምሮ ግፍና እንግልት ሲደርስባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

''በርካታ ኢትዮጵያውያንን የጨፈጨፈው የጣሊያኑ መሪ ግራዚያኒ የመታሰቢያ ሃውልትና ሙዚየም ሊሰራለት አይገባም'' በሚል በመቃወማቸው በህወሃት ለእስር ተዳርገው ድብደባና ከፍትኛ እንግልት እንደደረሰባቸው ኢንጅነር ጌታነህ ይናገራሉ።

''ህወሃት በሀሰት መወንጀልና ሀሰተኛ ማስረጃ ማደራጀት የተካነበት ልማዱ ነው'' የሚሉት ኢንጅነር ጌታነህ፤ በሀሰት ተወንጅለው ለከፋ እንግልት ተዳርገው እንደነበር ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በኢትዮጵያውያን ላይ ሲያደርስ የነበረው ሰብዓዊና ስነልቦናዊ ወንጀል በዓለም አቀፍ ወንጀል ተጠያቂ የሚያደርገው መሆኑን ይናገራሉ።

አሸባሪው የህውሃት ቡድን እስከመቼ ነው በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰው ግፍና በደል ዝም የሚባለው? ኢትዮጵያውያንስ እስከመቼ የሽብር ቡድኑን ተሸክመው ይኖራሉ? የሚል ጥያቄም ያነሳሉ ኢንጅነር ጌታነህ።

የሽብር ቡድኑን በተባበረ ክንድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት ካልተቻለ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚያደርሰው ግፍና መከራ ማቆሚያ እንደሌለውም ያነሳሉ።

አንዳንድ የውጭ መንግስታትና አለም አቀፍ ድርጅቶች ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት አሸባሪ ቡድኑን እየደገፉ መሆኑን እንዲሁ።

እነዚህ አካላት ከቡድኑ አመራሮች ጋር ባላቸው ጥቅመኝነት እየደገፉት በመሆኑ በአሸባሪ ቡድኑ የሚደርሱ ወንጀሎችን በዝምታ ማለፍ ይመርጣሉ ነው ያሉት።

የምዕራባውያንን ተጽዕኖ ለመቀነስ ድህነትን ማሸነፍ ቀዳሚው ተግባር መሆኑንም ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም