ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሃ-ግብር ተማሪዎችን ተቀብሎ ሊያስተምር ነው

ሐምሌ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሃ-ግብር ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደሚጀምር አስታወቀ።

ከ60 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ ተማሪዎችን በአብራሪነት፣ በአውሮፕላን ቴክኒሻንነት፣ በገበያና ፋይናንስ እንዲሁም በደንበኞች አገልግሎት መስክ እያሰለጠነ ይገኛል።

የአቪዬሽን አካዳሚው የአብራሪዎች ማሠልጠኛ፣ የአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሺያኖች፣ የበረራ አስተናጋጆችና የገበያ ባለሙያዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቶች አሉት።

የአካዳሚው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መሳይ ሽፈራው አካዳሚው በኮሌጅ ደረጃ ይገኝ እንደነበር ጠቅሰው፤ ከአንድ ዓመት በፊት ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በዩኒቨርሲቲነት ማስተማር የሚችልበትን ፈቃድ እንዳገኘ ተናግረዋል።

አካዳሚው ከጥር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በቅድመና በድህረ ምረቃ መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም አቶ መሳይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

'ባችለር ኦፍ ሳይንስ ኤሮናውቲካል ኢንጂነሪንግ'፣ 'ባችለር ኦፍ ሳይንስ ኤርክራፍት ሜንቴናነስ ኢንጂነሪንግ'፣ 'ባችለር ኦፍ ሳይንስ ኤርላይን ማኔጅመንት ኤንድ ኦፕሬሽን' እንዲሁም 'ባችለር ኦፍ ሳይንስ ኤርፖርት ማኔጅመንት' ዘርፎች በቅድመ ምረቃ መርሃ-ግብር ትምህርት ይሰጥባቸዋል።

አካዳሚው 'ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ኢን አቪዬሸን' በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ለማስተማር አቅዷል።

ለትምህርቱ የሚያስፈልግ የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ መጠናቀቁን ገልጸው፤ በዚህም በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ምዝገባ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅቶች መደረጉን ገልጸዋል።

በአካዳሚው ከሚገኙ ባለሙያዎች በተጨማሪ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራን እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከውጪ አገሮች አስተማሪዎችን በማስመጣት ትምህርቱን ለመስጠት መታቀዱንም አቶ መሳይ አመልክተዋል።

አካዳሚው በመጀመሪያው ዓመት እስከ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል ማቀዱን ገልጸዋል።

አካዳሚው ስያሜውን ወደ ኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ እንደሚቀየር የተናገሩት አቶ መሳይ፤ የዩኒቨርሲቲው አደረጃጀት ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ቀርቦ እስከ ጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የውጪ አገራት ዜጎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

አካዳሚው በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሃ ግብሮች የሚያስተምራቸውን የትምህርት አይነቶች በማሳደግ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ ለማስተማር እቅድ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

በቱሪዝምና መስተንግዶ ዘርፍ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመስጠት የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ እየተከናወነ እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።

"አካዳሚው በረጅም ጊዜ እቅዱ ተመሳሳይ ትምህርት ከሚሰጡ የሌሎች አገራት የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር የመስራትና ቅርንጫፍ የመክፈት እቅድ አለው" ብለዋል።

በዲፕሎማ ደረጃ የሚሰጠው ትምህርትና ስልጠናን እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ የሚሰጠው ትምህርትና ስልጠና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እ.አ.አ ከ2020 ጀምሮ ለ15 ዓመታት ተግባራዊ በሚሆነው የስትራቴጂክ እቅድ መሰረት ያደረገ እንደሆነም ነው አቶ መሳይ የሚያስረዱት።

በስትራቴጂክ እቅዱ የሰው ሃይል ልማት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ አካዳሚው በአቪዬሽን ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን አንስተዋል።

ከ60 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የአቪዬሽን አካዳሚው ከምስረታው አንስቶ ከ16 ሺህ በላይ ባለሙያዎችን ያስመረቀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ የሚሆኑት ከ48 በላይ አገሮች (አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ) የመጡ ሰልጣኞች ናቸው።

አካዳሚው በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ሲሆን፤ የቅበላ አቅሙንም እ.አ.አ በ2030 ወደ 4 ሺህ ከፍ የማድረግ እቅድ አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም