ማህበሩ ለቢራ ጠመቃ የሚጠቀምበት ውሃ ያለበትን አካባቢ ለማልማት ስምምነት አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ለቢራ ጠመቃ የሚጠቀምበት ውሃ ያለበትን አካባቢ ለማልማት ስምምነት አደረገ
ማይጨው ግንቦት 8/2010 ራያ ቢራ አክሲዮን ማህበር ለቢራ ጠመቃ የሚጠቀምበትን የከርሰ ምድር ውሃ አካባቢ ለማልማት ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡ በማይጨው ከተማ የሚገኘው የራያ ቢራ ፋብሪካ ለቢራ ጠመቃ የሚጠቀምበትን የከርሰ ምድር ውሃ የሚያገኘው በእንዳመኸኒ ወረዳ " ማይ ሙቅ " ከተባለ አካባቢ ነው፡፡ አክስዮን ማህበሩ ውሃ በሚጠቀምበት አካባቢ ያሉ አርሶአደሮችን ጨምሮ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድርግ ከተለያዩ አካላት ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡ በስምምነቱ በእንዳመኸኒ ወረዳ የመኸን ቀበሌ ገበሬ ማህበር አስተዳደር፣ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ፣ መቀሌ ዩኒቨርሲቲና የዓለም ባንክ በጋራ ተፈራርመዋል፡፡፡ የራያ ቢራ ፋብሪካ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ዶክተር ትካቦ ገብረስላሴ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ፋብሪካው " በማይ ሙቅ" አካባቢ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚያደርገው ፕሮጀክት የተፋሰስ ልማት፣ የደንና መስኖ ልማት ሥራዎችን በማጠናከር የሕብረተሰቡንና የፋብሪካውን ተጠቀሚነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያግዛል። ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚሆነው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲና የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ለልማቱ ሥራ የሚያስፈልግ አጠቃላይ ወጪ እንዲሁም ዝርዝር የሥራ አፈጻጸም የሚያሳይ የድርጊት መርሃግብርን አዘጋጅተው ሲያቀርቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚውለው ገንዘብ በአብዛኛው በፋብሪካው ለመሸፈን ዝግጅት መደረጉን የገለጹ ሲሆን፤የዓለም ባንክም ለፕሮጀክቱ የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱንም አመልክተዋል፡፡ “በፕሮጀክቱ አስር ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተፋሰስ ልማት ሥራ ይከናወናል” ያሉት ዶክተር ትካብ፣ የተፋሰስ ልማቱ የአካባቢው የተፈጥሮ ሀብትን ጠብቆ ለማቆየት እንደሚያስችል ገልጸዋል። ይህም ፋብሪካው የሚጠቀምበትን ውሃ ዘላቂ በማድረግ የአካባቢውንም ሕብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማጠናከር ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል። የክልሉን ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት በቢሮው የዘላቂ መሬት ሥራ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ መሀሪ ገብረመድህን ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት ስምምነቱ ኩባንያዎች በአካባቢ ብክለት ላይ ያላቸውን ድርሻ ለመቀነስና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ነው፡፡ ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት ሥራዎች በሚያካሂዱበት ቦታ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያነሳሳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ፣ ፋብሪካው በሚጠቀምበት ውሃ 110 አርሶ አደሮች የመስኖ ልማት በማካሄድና ሌሎች 16 አርሶ አደሮች በአፕል ልማት በመሰማራት ተጠቃሚ ሆነዋል። አካባቢውን ወደ ተሻለ ደረጃ በማድረስ የአካባቢው አርሶ አደሮች ከፕሮጀክቱ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚደረገው ጥረት ቢሮው የሙያ ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል፡፡ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት የዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ኪዳነ ግደይ ናቸው፡፡ "ዩኒቨርሲቲው ፋብሪካው የሚጠቀምበት የማይ ሙቅ ተፈጥሯዊ የከርስ ምድር ውሃ ከፋብሪካው ባለፈ አርሶአደሮችን በመስኖ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥናትና ምርምር ከማካሄድ ባለፈ ለግብርና ባለሙያዎች ስልጠና ይሰጣል" ብለዋል ፡፡ በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ካንትሪ ኦፊስ ዘላቂ የመሬትና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ፕሮግራም ባለሙያ ሚስተር ፓል ማርቲን በበኩላቸው እንዳሉት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚካሄዱ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የራያ ቢራ ፋብሪካ ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ያሳየውን ቁርጠኝነት ሌሎች የኢንቨስትመንት ተቋማትም ሊጋሩት እንደሚገባ ዶክተር ኪዳነ አስገንዝበዋል፡፡