ቀጥታ፡

የዲያስፖራ ትረስት ፈንዱ ቀጣይነት እንዲኖረው ግልፅነት የሰፈነበት ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት ይገባል - ምሁራን

አዲስ አበባ ነሀሴ3/2010 በኢትዮጵያ የተጀመረው የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ቀጣይነት እንዲኖረው መንግስት ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ጠንካራ ተቋማዊ አሰራር መፍጠር እንዳለበት የኢኮኖሚ ምሁራን ገለጹ። ትረስት ፈንድ ገንዘቡን የሚሰጥ፣ ገንዘቡን የሚቀበልና በመካከል ደግሞ ገንዘቡን የሚያስተዳድር ግለሰብ ወይም ተቋም ያለው አሰራር መሆኑ ይታወቃል። በተለያዩ አገራት የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ተቋማዊ አሰራር ተዘርግቶለት ከገንዘብም ባለፈ እውቀታቸውን እና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገራቸው በመላክ እንደመሰባሰቢያ ይጠቀሙበታል። እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ 2017 የአለም ባንክ ዘገባ በዓለም ላይ ከተለያዩ ተቋማት ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለእርዳታ መሰብሰቡን መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲን ዶክተር ካሳ ተሻገር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዓለም ላይ ከሶስት እስከ አራት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ውስን ነበር። መንግስትና ዲያስፖራው ለዓመታት በጥላቻና በመቃቃር ተለያይተው በመኖራቸው የነበረው ውስንነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የስራ ዘመን የጥላቻ ግንቡ ፈርሶ የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በመከፈቱ "የአንድነት ድልድይ ግንባታ ተጀምሯል" ብለዋል። በመሆኑም ዲያስፖራው የኢትዮጵያን እድገት በባለቤትነት ስሜት እንዲደግፍና የተጀመረው ትረስት ፈንድ ቀጣይነት እንዲኖረው መንግስት ገንዘቡ ምን ላይ እንደዋለ ለዲያስፖራው የሚያሳውቅበት ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመዋል። ግልፅነት የሰፈነበት ተቋማዊ አሰራር በመንግስትና ዲያስፖራው መካከል መተማመን በመፍጠር ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን ለአገራቸው ጥቅም እንዲያውሉት ከማድረግ በተጨማሪም የሌሎች አገራት ዜጎች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ  ለማነሳሳት ዋስትና ይሆናቸዋል ብለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ጊዲሳ ለቺሳ የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ መንግስት በአግባቡ ከተጠቀመበት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግና የኅብረተሰቡን ኑሮ ማሻሻል የሚያስችለው እንደሆነ ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ ፈንዱ ቀጣይነት እንዲኖረው መንግስት ቀድሞ ሊሰራቸው ያሰባቸውን ፕሮጀክቶች እንዲሁም ስራ ሲጀምር ውጤቶችን ያመጡትን ለውጥ በተጨባጭ ማሳየት የሚችልበት አሰራር ሊኖረው ይገባል ይላሉ። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ  የዲቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ መምህር አቶ መዚድ ናስር በበኩላቸው መንግስት አሁን ቃል የተገባውን ውስን ገንዘብ ሳይሆን በቀጣይ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ማስተዳደር እንዳለበት ታሳቢ አድርጎ መዋቅር መዘርጋት አለበት ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በገለጹት መሰረት ገለልተኛ ተቋም ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባት ካልቻለ የትረስት ፈንዱ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ላይ የሚኖረውን አስተዋፅኦ በመረዳት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን መደገፍ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥ የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ግልጽ አሰራር፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲና ቀጣይነት ያለው ሰላም መኖር አለበት ብለዋል። የዲያስፖራ ትረስት ፈንዱ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመቀነስ፣ የባለሃብቶችን ተሳትፎ በማሳደግና በዜጎች መካከል መቀራረብ በመፍጠር የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚለግሱትን ገንዘብ ለማሰባሰብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በሚል ስያሜ የሂሳብ ቁጥሩ 1000255726725 ሆኖ ከሐምሌ 2010ዓ.ም ጀምሮ ክፍት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም