ቀጥታ፡

የህወሃት አሸባሪ ቡድን ለመፋለም ለተዘጋጁ የአገር ባለውለታዎች ሁሉ ክብርና አድናቆት ይገባቸዋል - የገቢዎች ሚኒስትር

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለውን የህወሃት አሸባሪ ቡድን ለመፋለም ለተዘጋጁ የአገር ባለውለታዎች ሁሉ ክብርና አድናቆት ይገባቸዋል ሲሉ የገቢዎች ሚንስትር ላቀ አያሌው ተናገሩ፡፡

በክህደት እየተንቀሳቀሰ ካለው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የአገራቸውንና ህዝባቸውን ህልውና ለማስጠበቅ ወደ ዘመቻ የሚሄዱ አራት ሰራተኞቹን የገቢዎች ሚኒስቴር ሽኝት አድርጓል።


በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው፤ በራሳቸው ተነሳሽነት ለአገራችሁ ውድ ህይወታቸውን በመስጠት ወደ ዘመቻ ለማቅናት የተዘጋጁ ሰራተኞች ታላቅ የአገር ባለውለታ ናቸው ብለዋል፡፡ 

ከአሸባሪው የህወሃት ቡድን አገራቸውን ለመታደግ  ለዘመቻ የተዘጋጃችሁ "ጀግኖች ናችሁ፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ሲዘክረው ይኖራል" ብለዋል። 

ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለውን የህወሃት አሸባሪ ቡድን ለመፋለም ለተዘጋጁ የአገር ባለውለታዎች ሁሉ ክብርና አድናቆት ይገባቸዋልም ነው ያሉት።


ዘማቾች አገር ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ድል አድርጋችሁ እንደምትመለሱ "ፅኑ እምነት አለኝ” ሲሉም ተናግረዋል።


የሽብር ቡድኑን እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በዚሁ አጋጣሚ ዜጎች በየተሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለባቸው ያሉት አቶ ላቀ የሚኒስቴሩ ሰራተኞችም ገቢ የመሰብሰብ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ሊፋጠን የሚችለው ገቢ በአግባቡ ሲሰበሰብ በመሆኑ ሰራተኞች ትርፍ ጊዜያቸውንም ጭምር በመጠቀም የሚጠበቅባቸውን እንዲያከናውኑም አሳስበዋል፡፡

የህወሃት አሸባሪ ቡድን ለመፋለም ወደ ዘመቻ ለመሄድ የተዘጋጁ ሰራተኞችም ለአገራችን በመዝመታችን ኩራት ይሰማናል ብለዋል።


አሸባሪው የህወሓት ቡድን በህዝብ ላይ እያከናወነ ያለው ግፍ እና በደል እንዲሁም አገር ለማፍረስ እያከናወነው ያለው እኩይ ተግባር ለመዝመት እንዳነሳሳቸው ገልጸው በጀግንነት ተፋልመው በድል እንደሚመለሱም አረጋግጠዋል። 

ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዘመቻው ከተሸኙት አራት ሠራተኞች መካከል ሁለቱ ከአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ሠራተኞች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም