ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት የሀሰት መረጃዎችን በመልቀቅ ሽንፈቱን ለመደበቅና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት እየጣረ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2013(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት የሀሰት መረጃዎችን በመለቀቅ ሽንፈቱን ለመደበቅና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት እየጣረ ነው።

ቡድኑ ከማዕከላዊ መንግስት ስልጣኑን ካጣ ጀምሮ የተለያዩ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝቡንና ዓለምአቀፉን ማህበረሰብ የማደናገር ስራ እያከናወነ ይገኛል።

ቡድኑ የህዝብ ፕሮጀክት የሆነውን የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ "ግንባታው ተቋርጧል፣ ግድቡም ተሽጧል" የሚል የሃሰት መርዶ ነጋሪ መሆኑም ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

ጊዜው ሲደርስና ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ሙሌት ስታከናውን የቡድኑ የሀሰት መረጃ ተጋልጧል።

በአሁኑ ወቅት ቡድኑ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ታግደዋል፣ ተገድለዋልና ከድተዋል የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን ከማሰራጨት ባለፈ የተለያዩ ቦታዎችን መቆጣጠሩን ይገልጻል። እውነታው ግን ሌላ እየሆነ ይጋለጣል።

አሸባሪው ህወሃት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት ላይ ፍጹም ዘግናኝ የሆነ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ከፈጸማ በኋላ የፌዴራል መንግስት በወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ወቅት ያልሆነውን ሆኗል በማለት ለሽብር የሚዳርጉ የሀሰት መረጃዎችን በመገናኛ ብዙሃን ሲለቅ እንደነበር ይታወሳል።

የሀሰት መረጃ በተመለከተ ወጣቶች ሲናገሩ፤ አሸባሪው ቡድን የሀሰት መረጃዎችን የሚያሰራጨው ህዝቡንና ዓለምአቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት ነው።

ይህን የማሳሳት ዓላማውን በመገንዘብ "በእውነተኛ መረጃ ማጋለጥ ይገባል" ሲሉም ነው የሚናገሩት።  

በተለያዩ ጊዜያት ሲሰራጩ የነበሩ ሀሰተኛ መረጃዎች ጊዜያቸውን ጠብቀው እንደሚጋለጡ የህዳሴ ግድቡ አንዱ ማሳያ መሆኑን አስታውሰዋል።

ወጣት ወርቁ ፍቃዱ እንደገለጸው አሸባሪው ቡድን የህዳሴ ግድብ ቆሟል እና ሀገሪቱ ላይ ያልሆነውን ሀገር እንዲህ ሆነች በማለት ሲገልጽ እንደነበርና አሁን ያየው ትክክለኛው ነገር ውሸት ማሸነፍ እንደማይችል ነው። የሀገሪቱ ህዝብም ይሄን ተገንዝቦ በማህበራዊ ሚዲያ ከሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሊቆጠብ እንደሚገባም ወጣቱ መክሯል።   

አሸባሪው ቡድን በፊትም ጀምሮ ሌላ ሀገር ላይ የሆነን ኢትዮጵያ ላይ  እዚህ ቦታ  ሆነ ብሎ የሀሰት መረጃ ሲያሰራጭ መቆየቱን ተመልክተናል ያለው መምህር ብርሃኑ ተስፋዬ፤ እነዚህ መረጃዎች ሀገሪቱን በተለያየ መልኩ ጎድቷታል ነው ያለው። ድርጊቱ የሀገሪቱን ህዝብ የቆየ የመተባበርና አብሮነት እሴት  እንደጎና ተናግረው ማህበረሰቡ ያልተጣራና ሐሰተኛ መረጃን ከማጋራት  ራሱን ማራቅ አለበትም ብሏል። 

የአገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እንደሚሉት፤ የህወሃት ሽብር ቡድን "ውሸትና ማስመሰል" ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው።

የሽብር ቡድኑ በሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ሽብር ለመፍጠር የሚሞክረው የደረሰበትን ሽንፈት ለመደበቅ በማሰብ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

ይህ ደግሞ ሃላፊነት ከማይሰማውና እኩይ ዓላማ ካነገበ ቡድን የሚጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል።

ቡድኑ ያልተቆጣጠረውን ቦታ "ይዣለሁ" በማለትና በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሽብር ጥቃት ይፈጸማል የሚሉት የማስፈራሪያ ቅዠቶች የተለመዱ መሆናቸውን ይናገራል።

"አሸባሪው ቡድን ውሸትና ማስመሰል ተፈጥሯዊ ባህሪው በመሆኑ" ህዝቡ በዚህ ሳይደናገር በተጠናከረ ክንድ በአሸባሪው ሃይል ላይ መዝመት እንዳለበት ነው ኮሎኔል ጌትነት የጠቆሙት።

በማህበራዊ ሚዲያና በሌሎች የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ያልተረጋገጡ መረጃዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ግለሰቦችና ተቋማት ከዚሁ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብም "በሬ ወለደ" ለሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎች ጆሮ ባለመስጠት የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ታሪክ ማስቀጠል እንዳለበት ነው የተናገሩት።

ህብረተሰቡ የመረጃ ምንጩ ያልታወቀ ቀልብ የሚስቡና ታአማኒነት የሌላቸውን መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ተሰራጭቶ ሲያገኝ ከማጋራት መቆጠብ አስፈላጊ መሆኑም ነው አጽንኦት የሚሰጠው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም