የኤች.አይ.ቪ/ቫይረስ በደማቸው በሚገኝ ዜጎች ላይ አሁንም መገለልና አድልዎ ይፈፀማል - ኢዜአ አማርኛ
የኤች.አይ.ቪ/ቫይረስ በደማቸው በሚገኝ ዜጎች ላይ አሁንም መገለልና አድልዎ ይፈፀማል
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 26/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ በደማቸው የኤች.አይ.ቪ/ቫይረስ ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰው መድልዎና ማግለል አሁንም መቀጠሉን አንድ ጥናት አመላከተ።
ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝ ዜጎች ፍቅርና እንክብካቤ በመስጠት አምራች ዜጋ ማድረግ እንደሚገባም የሃይማኖት አባቶች አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የኤች.አይ.ቪ/ቫይረስ በደማቸው በሚገኝና በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰውን ማግለልና አድልዎ ለመቀነስ "ፈጣሪ አያገልም፣ አያዳላም፣ እኛም አናግል፣ አናዳላ" በሚል የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ላይ የሚደርሰው መድልዎና ማግለል አሁንም መኖሩን የሚያመላክት ጥናት ቀርቧል።
ጥናቱን ያቀረቡት ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ማኅበራት ጥምረት ተወካይ አቶ ጌታቸው ጎንፉ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሴተኛ አዳሪዎች፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና አደንዛዥ ዕጽ የሚጠቀሙና ቫይረሱ ያለባቸው በጥናቱ መካተታቸውን ገልፀዋል።
የጥናቱ ግኝት እንዳመላከተው መገለልና መድልዎን በመፍራት 78 በመቶ የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው እንዳለባቸው መናገር የማይደፍሩ ሲሆኑ 52 በመቶ ያህሉ ደግሞ ቫይረሱ እንዳለባቸው ይደብቃሉ።
ይህን አስተሳሰብ በመስበር የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና ቫይረሱ ያለባቸውም የሕክምና ክትትል በማድረግ ጤነኛና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ጠንካራ ስራ እንደሚጠየቅ ተመላክቷል።
ቫይረሱ እንዳለባቸው አውቀው መድሃኒት የጀመሩ ከዕምነት ጋር ይጋጫል በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ማቋረጥ ሌላው የሚስተዋል ችግር በመሆኑ የሃይማኖት አባቶች በዚህ ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።
በንቅናቄ መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የቫይረሱን መከላከያ መንገዶች በመተግበር ጤናን መጠበቅ እንደሚገባ መክረዋል።
በበሽታው ከተያዙም የሐኪሞችን ምክር በመከተል መድሃኒት መውሰድ እንደሚገባ፤ ቫይረሱ ላለባቸውም ፍቅርና እንክብካቤ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በዕምነታቸው መሰረት ፀበል የሚጠቀሙም ለቫይረሱ ከሚወሰድ መድሃኒት ጋር የማይጋጭ በመሆኑ ሁለቱንም ጎን ለጎን መጠቀም እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተወካይ ሼክ ቃሲም ሼህ መሃመድ ታጁዲን በዕምነቱ የተከለከለውን ከጋብቻ ውጭ ግንኙነት ባለመፈጸም የቫይረሱን ስርጭት መግታት ይገባል ብለዋል።
የዕምነት ተቋማት ማግለልና መድልዎ ባለማድረግ በቫይረሱ የተያዙ ዜጎችን ፍቅርና እንክብካቤ በመስጠት አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ዓርአያ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል "ፈጣሪ አያገልም፣ አያዳላም፣ እኛም አናግል፣ አናዳላ" ፍቅር እንስጥ ሲሉ ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶችም ተመሳሳይ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስና መድልዎና ማገለልን ለማስቀረት ግንዛቤ በመፍጠር ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የመድሎና ማግለል ጉዳይ ትልቅ ትኩረት እንደሚሻና በተጨማሪም የበለጠ ድጋፍ መስጠት፣ የማኅበራዊና የስነ-ልቦና ድጋፍ ማድረግ ከሁሉም በተለይም ከዕምነት ተቋማት የሚጠበቁ ተግባራት እንደሆኑ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ስርጭት ምጣኔ 0 ነጥብ 88 እንደሆነ፤ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ቁጥርም 600 ሺህ መድረሱ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 2030 ኤች.አይ.ቪ ማኅበራዊ ችግር ሆኖ እንዳይቀጥል እቅድ ይዛ እየሰራች ትገኛለች።