በኢትዮጵያ 97 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት በማጥባት ያሳድጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ 97 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት በማጥባት ያሳድጋሉ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 26/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ 97 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት በማጥባት እንደሚያሳድጉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደስ ዓለም አቀፍ የጡት ማጥባት ሳምንትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የኢትዮጵያ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት አጥብተው በማሳደግ የተሻለ ልምድ እንዳላቸው አንስተዋል።
ሆኖም ብዙዎቹ እናቶች የሚያጠቡበት ሁኔታ የግንዛቤ ክፍተት ያለበት በመሆኑ በቀጣይ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል።
ህፃናትን ጡት በማጥባት የማሳደግ ሂደት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
የእናት ጡት ወተት ህፃናት በበሽታ እንዳይጠቁ እና ጠንካራ ሆነው እንዲያድጉ ያስችላቸዋል ብለዋል።
የእናት ጡት ወተት በውስጡ ያለው ንጥረ ነገር የልጆችን አካላዊና አዕምሯዊ እድገት ጥሩ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።
የእናታቸውን ጡት ጠብተው ያደጉ ልጆች በአዋቂነት ዕድሜያቸው ተላላፊ በሽታዎችን በተሻለ መልኩ የመከላከል አቅም እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል።
ዓለም አቀፉ ጡት የማጥባት ሳምንት “ጡት ማጥባትን መጠበቅ፣ የጋራ ሃላፊነት!!” በሚል መሪ ሃሳብ ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።
የዘንድሮው የጡት ማጥባት ሳምንት በዓለም ለ30ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ13ኛ ጊዜ ይከበራል።