የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ ደንብ ልብስ ተቀየረ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ ደንብ ልብስ ተቀየረ
ሀዋሳ፣ ሐምሌ 26/2013 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ ደንብ ልብስ ከዛሬ ጀምሮ መቀየሩን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ይፋ አደረገ።
የክልሉ ምክር ቤት አባላትና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው በተገኙበት ኮሚሽኑ አዲሱን የደንብ ልብስ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የደንብ ልብስ መቀየሩን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀ ስነ ስርአት ላይ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነብዩ ኢሣይያስ እንዳስታወቁት ደንብ ልብሱን መቀየር ያስፈለገው ባለፉት ዓመታት የክልሉ ፖሊስ የተጣለበትን ግዳጅ ሲወጣ ለብሶት የነበረው የደንብ ልብስ ሰራዊቱን የማይመጥንና ጥራት የጎደለው በመሆኑ ነው።
በተለይ ደንብ ልብሱን ሲያመርት የነበረው ድርጅት በተለያየ አሻጥር በመመሳጠር ልብሱን ለሌሎች ባዕድ አካላት አምርቶ በማሰራጨት ሰራዊቱንና ህዝቡን ለጥቃት ሲያጋልጥ በመቆየቱ ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል።
የቀድሞ ደንብ ልብስ ለሌሎች አካላት ተመርቶ በመሰጠቱ በግዳጅ አፈፃፀም ወቅት ከፍተኛ ችግር ሲያስከትል እንደነበር ጠቁመው ከችግሩ ለመላቀቅ ለክልሉ መንግሥት በማሳወቅ ፈጣን ምላሽ መደረጉን ተናግረዋል።
አዲሱ የደንብ ልብስ ሰራዊቱን የሚመጥንና ለግዳጅ ዝግጁ እንደሚያደርገው ገልጸው ከዚህ በኋላ የቀድሞው የደንብ ልብስ አገልግሎት ላይ እንደማይውል አስታውቀዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የልዩ ኃይል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር እንዳለ አበራ በበኩላቸው ላለፉት10 ዓመታት ያገለገለው የደንብ ልብስ የተቀየረበት ሌላው ምክንያት ከሰራዊቱ የሚከዱ፣ የሚወጡና የሚቀነሱ አባላት ደንብ ልብሱን ይዘው ስለወጡ ህገ ወጥ ሰዎች እጅ በመግባቱ የሚፈጸመውን ወንጀል ለመከላከል መሆኑን አስረድተዋል።
ከክልሉ ልዩ ኃይል አባላት መካከል ረዳት ኢንስፔክተር የምስራች በላቸው በሰጠችው አስተያየት የቀድሞ ደንብ ልብስ ለግዳጅ አፈጻጸም አመቺ እንዳልነበረ ገልጻለች።
በተለይ ልብሱ በፀረ ሰላም ኃይሎች እጅ በመግባቱ ሰራዊቱንና ህገ ወጡን ለመለየት አስቸጋሪ በመሆኑ ሠራዊቱ ፀጥታውን ባለቤት ሆኖ ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ እስከ መስዋዕት ዋጋ ማስከፈሉን ጠቅሳለች።
"አዲሱ የደንብ ልብስ ሠራዊቱን ከስጋት በማላቀቅ በየትኛውም አየር ፀባይ የተጣለብንን ግዳጅ ለመወጣት ያስችላል" ብላለች።
በስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የፖሊስ ኃይሉን ማጠናከር የክልሉን ህዝብ ደህንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
"የፖሊስ ሀይሉን በማጠናከር እረገድ ከለውጡ ወዲህ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም በቂ አይደሉም" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የፖሊስ ኃይሉን በሰው ሃይልና በቁሳቁስ ከማጠናከር ባለፈ ለሚከፍለው መስዋእትነት እውቅና እንዲያገኝ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።