ኢትዮጵያን በከፍተኛ ጭቆና ሲመራ የቆየው ህወሃት በአሁኑ ወቅትም በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ እንዳይደርስ እያደረገ ነው - አትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን በከፍተኛ ጭቆና ሲመራ የቆየው ህወሃት በአሁኑ ወቅትም በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ እንዳይደርስ እያደረገ ነው - አትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል
ሐምሌ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) "ከሁለት አስርታት በላይ ኢትዮጵያን በከፍተኛ ጭቆና ሲመራ የቆየው ህወሃት በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለትግራይ ክልል የሚደረጉ የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎችን በማደናቀፍ ድጋፍ እንዳይደርስ እያደረገ ነው" ሲሉ የአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ብሮንዊን ብሩተን ገለጹ።
የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታዎችን በተመለከተ ከቢቢሲ ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት ብሮንዊን ብሩተን “በክልሉ አሁን ላይ የሰብአዊ ድጋፍ መስተጓጎል እንዲገጥም ያደረገው አሸባሪው ህወሃት ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ያወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም ባለመቀበል አሸባሪው ድርጅት ውጊያ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀው፤ ለትግራይ ክልል የሚደረገውን የሰብአዊ ድጋፍ እያደናቀፈ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
ምክትል ዳይሬክተሯ አክለውም “አጎራባች አማራና አፋር ክልሎች ላይ ድርጅቱ ባደረገው ጥቃት ዜጎች ተፈናቅለዋል” ብለዋል።
በሌላ በኩል ሽብርተኛው ህወሃት ላለፉት 30 አመታት ገደማ አገሪቷን በአምባገነንነት መግዛቱን ገልጸው፤ የለውጡ ሂደት ከመጣ በኋላ ህወሃት የትግራይ ክልል በማስተዳደር የጦርነት ቅስቀሳ ሲያደርግ ቆይቶ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ሽብርተኛው ቡድን ጥቃቱን በማጠናከር በድጋሚ ወደ ስልጣን ለመምጣት ጦርነት መጀመሩን አመልክተው የፌደራል መንግስትም ይህንን ተከትሎ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ መግባቱን ገልጸዋል።
በአሸባሪው ቡድን አገዛዝ ምክንያት ከሁለት አስርታት በላይ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ጭቆና፣ በፍርሃትና በማንነታቸው ጥቃት ውስጥ እንደነበሩ ምክትል ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።