ቀጥታ፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማት ሀላፊዎችና ሰራተኞች በኮንሶ የ14 አቅመ ደካሞችን ቤት ጥገና ስራ አስጀመሩ

አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 25/2013 (ኢዜአ ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ሀላዎችና ሰራተኞች በኮንሶ የ14 አቅመ ደካሞችን ቤት ጥገና ስራ አስጀመሩ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማትና ከደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን በኮንሶ ዞን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ትላንት አካሂዷል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት ሀላፊዎችና ሰራተኞች ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር የ14 አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ጥገና ስራ አስጀምረዋል ።

ሀላፊዎቹና ሰራተኞቹ ለአቅመ ደካሞች ቤት መልሶ ግንባታ የሚውል 400 ኩንታል ሲሚንቶና 400 የጣራ ክዳን ቆርቆሮ በስነ ስርአቱ ላይ በድጋፍ አበርክተዋል።

በዞኑ ካራት ከተማ በካሞሌ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ሺህ በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከል የ14 አቅመ ደካሞች ቤት ጥገናን በይፋ አስጀምረዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የንግድ አሠራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው በእርከን ሥራና በመልክአ ምድር በዓለም ቅርስነት በመመዝገብ የኢትዮጵያ ስም በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ወዳደረገው ኮንሶ ዞን በመምጣታቸው ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀግብር ለማከናወንና የአቅመ ደካሞችን  ቤት በመጠገን ወገንተኝነታቸውን ለማሳየት መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

በካሞሌ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪ ክፍሎች እጥረት ለማቃለል ደረጃውን የጠበቀ አንድ ብሎክ ህንፃ ገንብቶ ለማስረከብ ቃል ገብተዋል።

"የብልጽግና ጉዟችን እዉን እንዲሆን እርስ በርስ በመተጋገዝ ተያይዘን ማደግ ይገባናል" ያሉት  ሚኒስትር ዴኤታው የኮንሶ ዞን ህዝብ ለሚያመርተው ምርት ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማየትና ተገቢዉን ድርሻ ለመወጣት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ወደ ኮንሶ ዞን ህዝብ በመምጣት ላሳዩት አጋርነት አመስግነዋል፡፡

ሀላፊዎቹና ሰራተኞቹ አረንጓዴ አሻራቸውን ከማኖር በላይ ችግረኞችን በመትከል ኢትዮጵያዊ ወገንተኝነትን በማሳየታቸው መደሰታቸውን በመግጽ "ለህዝቡ አብሮነትና አንድነት ተምሳሌት የሚሆን ተግባር ፈጽማችኋል" ሲሉ አድናቆታቸውን ችረዋል።

ህዝቡ ተሞክሮውን በመውሰድ በያለበት ስፍራ ከመንግስት አካላት ጋር በመቀናጀት የወገን አለኝታነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

"ባለቤቴንና አንድ ወጣት ልጄን በሞት በመነጠቄ ያለ ረዳት እኖራለሁ" ያሉት ደግሞ በኮንሶ ዞን የካራት ከተማ ነዋሪና የ85 ዓመት አዛውንቷ እማማ አይሊቶ ጎባሃዴ ናቸው።

በደሳሳ ጎጇቸው ዝናብና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው ተስፋ ቆርጠው በሚኖሩበት ወቅት ጎጇቸውን የሚጠግን ወገን በማግኘታቸው ደስታቸውን በእልልታ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም