ቀጥታ፡

የአሸባሪው ህወሃትን ሴራና የውጭ ጫናን በማክሸፍ የአገር ሉዓላዊነት ይከበራል

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 25/2013(ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሃትን ሴራ በማክሸፍ እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን ጫና በመከላከል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ህዝቡ ከመንግስት ጎን መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው።

በትግራይ ክልል ውስጥ ሆኖ የአገሩን ዳር ድንበር ሲያስከብር፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ማህበራዊ ድጋፎችን ሲያደርግ በቆየው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ህወሃት በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም የማይቻል ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ፈጸመ። 

የፌዴራል መንግስት የተፈጸመው ድርጊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተዳፈረ፣ ዋነኛውን ቀይ መስመር ያለፈ መሆኑን በመግለጽ የህግ ማስከበር ዘመቻ ማካሄድ ጀመረ። 

እርምጃውን በጀመረ በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የአሸባሪውን ሕወሃት አከርካሪ በመስበርና ታጣቂውን በመደምሰስ መቀሌ ከተማን ተቆጣጠረ።

መንግስት በክልሉ ህግ ለማስከበር ከሚወስደው እርምጃ ጎን ለጎን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም የመልሶ ግንባታ ስራ ሲያከናውንም ቆይቷል። 

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለትግራይ አርሶ አደር የክረምት ጊዜ ሳያልፍ የእርሻ ስራውን እንዲያከናውንና የጥሞና ጊዜም እንዲኖረው የተኩስ አቁም እንዲደረግ የፌዴራል መንግስትን ጠይቋል።

የፌዴራል መንግስትም ጥያቄውን ተቀብሎ የተኩስ አቁም ያደረገ ሲሆን፤ አሸባሪው ህወሃት ከገባበት ዋሻ በመውጣት አጎራባች ክልሎች ላይ ትንኮሳ በመፈጸም ጸብ እየጫረ ይገኛል።

ይህ ድርጉቱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንዳለመ ስለሚያረጋግጥ መላው ኢትዮጵያዊያንን በማስቆጣት “ከአገሬ በፊት እኔን” በማለት እንዲነሳ አድርጎታል። 

ለትግራይ ህዝብ የማያስበው አሸባሪው ቡድን ውሳኔውን ባለመቀበል በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በኩል ትንኮሳ ያደርጋል፤ የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ይነዛል።

የአሸባሪው ህወሃት ትንኮሳ ኢትዮጵያን ለማዳከምና መጠነ ሰፊ ግጭት ውስጥ እንድትገባ ለማድረግ ያለመ መሆኑ በተግባሩ አረጋግጧል። 

ለዚህ ምላሽ ደግሞ የክልል መንግስታት በጸጥታ ሃይል፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በሌሎች ድጋፎች የአገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በአንድ ላይ መቆማቸውን እያሳዩ ናቸው።

በአገራቸው ሕልውና ላይ ድርድር የማያውቁት ኢትዮጵያውያን ከወጣት እስከ አዛውንት የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በህግ ማስከበር ወቅት ሲያደርጉት እንደነበረው የመከላከያ ሠራዊትን በመደገፍ ከመንግስት ጎን መሆናቸውን ገልጸዋል። በተግባርም እያስመሰከሩ ናቸው።

ቡድኑ እስኪደመሰስ ድረስ በሙያ፣ በአይነት፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ደም በመለገስ፣ ግንባር ድረስ በመሄድ መከላከያ ሠራዊት ጎን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ አንድነትን አባቶቻቸው ጠብቀው እንዳቆዩት ሁሉ የአሸባሪውን ህወሃት ሴራ በማክሸፍ የአገር ሉዓላዊነትን እንደሚያስጠብቁ ነው የሚናገሩት።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በአንድነት ለማስከበር አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ  በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እየገለጹ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም