ቀጥታ፡

በሃገር ህልውና ላይ የመጣው የህወሃት አሸባሪ ቡድን ላያንሰራራ የሚደመሰሰው አሁን ነው

ደባርቅ ፤ ሐምሌ 25/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያውያን ህልውና ላይ የተደቀነውን የህወሓት ጁንታ ዳግመኛ እንዳያንሰራራ አድርጎ ለመደምሰስ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የጀመሩት ዘመቻ በስኬት እንደሚጠናቀቅ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያለዓለም ፈንታሁን ገልጸዋል።

ዋና አስተዳዳሪው ህብረተሰቡ ለሃገር መከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

አቶ ያለዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የአሸባሪው የህወሓት ቡድን "ህዝብን እንደ ህዝብ አጠፋለሁ ሃገርን እንደ ሃገር አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳ የእኩይ ሴራ ባለቤት ነው።"

"ይህ ቡድን በዓለም ላይ አሉ የሚባሉ እጅግ አስከፊና ዘግናኝ ወንጀሎችን በሰው ልጆች ላይ በመፈፀም ያውም በዜጋው ላይ ተስተካካይ የማይገኝለት ሃይል ስብስብ ነው" ብለዋል።

"የሃገሪቱ መሪ ሆኖ ቆይቶ እያለ ሃገሪቱን መልሶ የወጋ፣ ለውጭና ለውስጥ ጠላት አጋልጦ የሰጠ እጅግ መሰሪና ሰይጣናዊ ባህሪ የተጠናወተው አሸባሪ ቡድን" እንደሆነም ተናግረዋል።

እንዲሁም ለሽፍትነት ስራው አልመች ያሉ ንፁሃንን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል ዓለም አቀፍ ህጎችን በጣሰ አግባብ የሰብዓዊ ጥሰት እየፈፀመ እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል።

በእብሪት ተነሳስቶ የከፈተውን ጥቃት ለመመከትና ከምድረ ገፅ ደምስሶ በማጥፋት ዳግም እንዳይነሳ ለማድረግ ተገቢው ስራ እየተከናወነ እንደሆነም አመልክተዋል።

ለትግራይ ህዝብ ሲባል መንግስት የወሰደውን የጥሞና ጊዜ ተጠቅሞ የህወሃት አሸባሪ ቡድን በተለያዩ ግንባሮች ትንኮሳ እየፈጸመ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅትና ምላሽ እየተሰጠ ነው" ብለዋል።

የአሸባሪው ህወሃት ህልም ሃገርን ማፍረስ ቢሆንም የበለጠ ኢትዮጵያዊ አንድነትና ትብብር የተንፀባረቀበት እንዲሁም ህዝቡ የህወሃትን አፍራሽ ሴራ ይበልጥ እንዲረዳ ያደረገበት እንደሆነም ገልፀዋል።

ህዝቡ በግንባር ለሚገኘው ሰራዊት በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ተገቢውን ሎጀስቲክስ በማቅረብ ከፍተኛ የደጀንነት አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የህወሃት ትርፍራፊ ሃይልን በአጭር ጊዜ ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን የደጀንነት ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ያለዓለም ጥሪ አድርገዋል።

ለህግ እንቆማለን የሚሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ጉዳዩን እንዳላዩ ከማለፍ ወጥተው አሸባሪው ቡድን እየፈፀመ ያለውን ጥፋት ከምንጩ በመረዳት በዓለም አቀፍ ህግ እንዲጠየቅ እንዲያደርጉ መስራት እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም