የወልድያ ከተማ ሕዝብ ላደረገልን ድጋፍ እናመሰግናለን - ኢዜአ አማርኛ
የወልድያ ከተማ ሕዝብ ላደረገልን ድጋፍ እናመሰግናለን
ወልድያ 25/11/2013 (ኢዜአ ) አሸባሪው ትህነግ በከፈተው ጦርነት ከራያና አካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖች የወልድያ ከተማ ሕዝብ ላደረገላቸው ድጋፍ አመሰገኑ።
ከራያ ቆቦ ወረዳ ከሮቢት ከተማ የመጡት ወይዘሮ ጉዝጉዝ ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት ትህነግበከፈተው ጦርነት ቤታቸውን ዘግተው መቀየሪያ ልብስ እንኳን ሳይዙ በእግር ተጉዘው ወልድያ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ከነቤተሰባቸው አካባቢያቸውን ጥለው እንደወጡ የተናገሩት ወይዘሮ ጉዝጉዝ የወልድያ ህዝብ የእለት ምግብ፣ ውሀና አልባሳት እያቀረበላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቤታቸው ውስጥ ያመረቱት እህል፣ የተዘጋጀ ሽሮና በርበሬ እንዲሁም ሙሉ የቤት ቁሳቁስ ጥለው መውጣታቸውን ጠቁመው በቀጣይ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።
ሌላዋ ከራያ አካባቢ የመጡት ወይዘሮ ሙዘይን እሸቱ በበኩላቸው ጦርነቱ ሲከፈት ህጻን ልጃቸውን አዝለው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
እርሳቸው ወደ ወልድያ ከመጡ በኋላ በቤታቸው ያለ ሃብትና ንብረት በጁንታው ታጣቂዎች መዘረፉን መስማታቸውን ገልጸዋል።
የወልድያ ህዝብ ከምግብና ውሀ በተጨማሪ አልባሳት እየሰጣቸው መሆኑን ጠቁመው ሰላም ሰፍኖ ወደ አካባቢያቸው ሄደው እስኪቋቋሙ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
የቆቦ ወረዳ ቀበሌ 44 ነዋሪ ወጣት መሀመድ ዘውዱ ለግል ጉዳይ አዲስ አበባ ሄዶ ሲመለስ አካባቢው በጁንታው ሀይሎች ተወሮ መግቢያ በማጣቱ ወደ መጠለያ መግባቱን ተናግሯል።
ባለቤቱ ከነ ሁለት ልጆቹ ጨምሮ የቤት እንስሳትና ሌሎች ሃብትና ንብረት ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አለመቻሉን ጠቁሞ የወልድያ ህዝብ በመጠለያ ላለው ተፈናቃይ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግኗል።
በወልድያ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት የወጣቶች ዋና አማካሪ ወይዘሪት ነፃነት አምበሳው በበኩሏ ከራያ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡ 4ሺ604 ተፈናቃዮች በመጠለያ መኖራቸውን ተናግራለች።
ተፈናቃዮቹ በአራት ትምህርት ቤቶች ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጻለች ።
በግለሰቦች ቤት ተጠልለው የሚገኙም መኖራቸውን ጠቁማ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አመልክታለች።
የወልድያ ነዋሪ ለተፈናቃዮች የእለት ቀለብ ሲያቀርብ መቆየቱን ጠቁማ አሁን ላይ በዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና በኩል ምግብና ምግብ ነክ እንዲሁም ማብሰያ ቁሳቁስ በመቅረቡ ተፈናቃዮች ራሳቸው አብስለው እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን አስታውቃለች።