ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ132 ሺ ዶላር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ132 ሺ ዶላር በላይ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25/2013 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ ታስቦ በተሰራው ዘመናዊ የሃብት ማሰባሰቢያ ሥርዓት አማካኝነት 132 ሺ ዶላር ተሰበሰበ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ዘመናዊ የሃብት አሰባሰብ ሥርዓት ላይ ትኩረት አድርጓል።
የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሃይሉ አብረሃ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ለግድቡ ድጋፍ ማድረጋቸው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚያደርጉትን ድጋፋ ለማሳለጥና ቀልጣፋ ለማድረግ ዘመናዊ የሃብት አሰባሰብ ሥርዓት ላይ ትኩረት ተደርጎ የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል።
በቅርቡም ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ ገጽ መተግበሪያ በኢትዮጵያዊያን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በልጽጎ ይፋ ሆኗል።
መተግበሪያው በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚኖሩበት ቦታ ሆነው እንደ አቅማቸው የፈለጉትን የገንዘብ መጠን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችላቸው ነው።
ይሄው በገንዘብ ሚኒስቴር፣ ብሄራዊ ባንክና ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዕውቅና የተሰጠው የwww.mygerd.com የገንዘብ ማሰባሰቢያ ድረ-ገጽ፤ በቀላልና አስተማማኝ መንገድ ከፈቃደኛ ለጋሾች ለግድቡ ገንዘብ ማሰባሰብ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
ድረገጹ በኢትዮጵያ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በኩል እውቅና ያለውና ድጋፍ ሰጭውን የማያጠራጥር ዘመናዊ ሥርዓት ሲሆን፤ በዚሁ የድረ ገጽ ዘመናዊ የሀብት ማሰባሰብ መንገድ እስከአሁን ከ1ሺ27 ለጋሾች 132 ሺ ዶላር መሰብሰብ ተችሏል።
ኤሌክትሪክ ኃይል ቻፓ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ በተሰኘ የወጣት ኢትዮጵያዊያን የቴክኖሎጂ ድርጅት ጋር በመተባበርበ በነጻ እንዲበለጽግ ማድረጉ ይታወሳል።
የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሃይሉ እንደገለጹት፤ ከዚህ ጎን ለጎን የቴሌብር የሃብት ማስባሰቢያ ከተከፈተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 30 ሺ ብር ተሰብስቧል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ15 ቢሊዮን 729 ሚሊዮን ብር በላይ ከሕዝቡ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
ህዝቡም በቀጣይ ድጋፉን አጠናክረው እንዲቀጥል ሃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።