ቀጥታ፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ የአየር ወለድ ሠራዊት አባላት መንግስት የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 25/2013 (ኢዜአ) የቀድሞ የኢትዮጵያ የአየር ወለድ ሠራዊት አባላት አሸባሪውን የሕውሃት ቡድንን ለመደምሰስ መንግሥት የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።

የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ ሠራዊት ማኅበር ዛሬ በቢሸፍቱ ባካሄደው መርሃ ግብር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም ገልጿል።

የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከውስጥም ከውጭም ጦርነት ታውጆባታል።

ይህንንም ተከትሎ ቀድሞ የሠራዊቱ አባላት ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር ለመመከትና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር  የአቅማቸውን ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ከቀድሞ ሠራዊቱ አባላት መካከል አቅም ያላቸው ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀታቸውን አመልክተው፤ አቅም የሌላቸው ደግሞ አስፈላጊውን ሙያዊ ሥልጠና ለመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ቀሪው ደግሞ መንግሥት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ አስተዋጽዖ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የቀድሞ ሠራዊት ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ መስዋዕትነት መክፈሉን ገልጸው፤ አሁንም "አገር ሲፈርስ ቁጭ ብሎ ማየት አይችልም" ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጥቅም ለመሸጥ እየሰራ እንደሆነ ጠቁመው፤ ሕዝቡም ይህንን እኩይ ተግባር ለመመከት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።

የማኅበሩ ምክትል የበላይ ጠባቂ ኮሎኔል ታምሩ ኃይሉ በበኩላቸው፤ የቀድሞ ሠራዊት በአውደ ውጊያ የራሱ የሆነ ክህሎትና ብቃት ያለው መሆኑን አስታውሰዋል።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩ በርካታ ጥቃቶችን በመመከት ብርቱ ክንድ ማሳየቱን ገልጸው፤ አሁንም ይህንን ጀግንቱን እንደሚደግመው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም