የሕወሓት ጥፋት ቡድን በንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት በተጠናከረ የአንድነት ስሜት ማክሸፍ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሕወሓት ጥፋት ቡድን በንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት በተጠናከረ የአንድነት ስሜት ማክሸፍ ይገባል
ጭሮ፣ ሐምሌ 25/2013-(ኢዜአ) ..የህወሓት የጥፋት ቡድን በህዝብና በሀገር ሀብት ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት በተጠናከረ አንድነት ማክሸፍ ይገባል ሲሉ የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ መምህራን አስታወቁ።
ህብረተሰቡ አጥፊው ቡድን በሚያስተላልፋቸው የሀሰት መረጃዎች ሳይታለል የገጠመውን ፈተና በብቃት ሊወጣ እንደሚገባ ምሁራኑ አስገንዝበዋል።
የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኢብሳ አህመድ ለኢዜአ እንዳሉት በትግራይ ክልል የነበረው የፀጥታ አስከባሪ ሃይል ለቆ መውጣትና የተናጥል ተኩስ አቁም መታወጁን ተከትሎ አሸባሪው ህወሓት በአፋርና አማራ ክልል ንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ጥቃት ከስህተቱ አለመመለሱን የሚያሳይ ነው፡፡
"የክልሉ ምሁራንና ህብረተሰብ ክፍሎች በጥሞና ጊዜው ሰላም እንዲሰፍን ምክክር ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ የጥፋት ሃይሉ የነገ ሀገር ተረካቢ ታዳጊዎችን ለግል ፍላጎቱ ብሎ ለጦርነት ማሰማራቱ ትውልድ አጥፊ መሆኑን ያሳያል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር ለማፍረስ የሚመጣ አጥቂን ለመመከት እንግዳ አለመሆኑን የገለጹት ዶክተር ኢብሳ የቡድኑን እኩይ ሴራ በተጠናከረ አንድነት ማክሸፍ እንደሚገባ አመልክተዋል ።
"መንግስት ህዝቡን የሚያደናግሩ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩትን ተከታትሎ ለህግ ማቅረብና ያለውን እውነታ ለዓለም ህዝብ ማሳወቅ ይጠበቅበታል" ብለዋል።
"ጥቅማቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ ማስጠበቅ የሚፈልጉና የህዳሴው ግድብ ግንባታ እንዲደናቀፍ የሚሹ አካላትን ሴራ በማክሸፍ ሀገርን ከጥፋት ማዳን ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።
የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ህክምና አገልግሎት ባለሙያ አቶ አያሌው አባተ ህብረተሰቡ ውዥንብር ከሚፈጥሩ የሀሰት መረጃዎች ራሱን በመጠበቅና በተጠናከረ የአንድነት መንፈስ የተጋረጠበትን ፈተና ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።