ለግል ጥቅሙ በቆመው አሸባሪ የህወሓት ቡድን ሀገር አትፈርስም - ኢዜአ አማርኛ
ለግል ጥቅሙ በቆመው አሸባሪ የህወሓት ቡድን ሀገር አትፈርስም
ሐምሌ 25/2013(ኢዜአ) ለግል ጥቅሙ በቆመው አሸባሪ የህወሓት ቡድን ሀገር አትፈርስም ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ በኦሮሚያ ክልል የኢሉ አባቦር ዞን ወጣቶች ይገልጻሉ።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ዘመቻ ለመመከት ወጣቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን እየተቀላቀለ ይገኛል።
በፍቃዳቸው መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ሁለተኛ ዙር ሽኝት እየተጠባበቁ ያሉ የኢሉ አባቦር ዞን ወጣቶችም "እኛ እያለን ለግል ጥቅማቸው በቆሙ የህወሓት ቡድኖች ሀገር አትፈርስም" በሚል ወኔ ተነሳስተው በህልውና ዘመቻው ለመሳተፍ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል ።
ኢዜአ ካነጋገራቸው የዞኑ ወጣቶች መካከል በመቱ ወረዳ የ12ኛ መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ያለው የአሌ ቡያ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ጀማል ደኑ ከሀገር በላይ ምንም ነገር ስለሌለ መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል መወሰኑን ይገልጻል።
ተማሪ ጀማል “ሉዓላዊቷና ታሪካዊት ሀገሬ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ በሚፈልጉ ጠላቶቿ አትፈርስም” በማለት በዚህ ፈታኝ ወቅት በታማኝነት ሊቆምላት ቆርጦ መነሳቱንም ገልጿል።
አባቶቻችን ህይወታቸውን የገበሩላት የሀገር ፍቅር ስሜት ዛሬም በኛ በልጆቻቸው ውስጥ አለ" ያለው ደግሞ ወጣት ሲሳይ ታሲሳ ነው፡፡
“ሀገሬን በውስጥና በውጭ ሆነው ከሚያሴሩባት ጠላቶቿ ለመታደግና የአባቶችን የጀግንነት ታሪክ ለማስቀጠል እኔም ለመዝመት ተዘጋጅቻለሁ” ብሏል።
ከሀገር መከላከያ ጎን በመቆም ሀገርን የማዳን ድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ አልሞ የተነሳውን የጁንታውን ኃይል ለመደምሰስና የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከመከላከያ ጎን ለመሰለፍ በቁርጠኝነት መነሳቱንም ነው ያስታወቀው።
"ሀገርን ከጥፋት ለማዳን በሚደረገው ትግል ውስጥ የፊት ተሰላፊ ለሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንደ ወረዳ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት ደግሞ የመቱ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተካልኝ አበራ ናቸው።
ለህልውና ዘመቻው በሁለተኛው ዙር ድጋፍ እስካሁን ከ280 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡን ለአብነት ጠቅሰዋል ።