የጁንታውን ርዝራዥ ለመደምሰስ የሚካሄደውን ዘመቻ እንደግፋለን... የትግራይ ተወላጆች

ድሬዳዋ፤ሐምሌ 24/2013(ኢዜአ) ትግራይን ያለትውልድ ለማስቀረትና ሀገርን ለማፍረስ እየጣራ ያለውን አሸባሪው የህውሃት ጁንታ ርዝራዥ ለመደምሰስ የሚካሄደውን ዘመቻ እንደግፋለን ሲሉ በድሬዳዋ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ተናገሩ።

አሸባሪው ቡድን ህጻናትን በጦርነት በመማገድ በአለም አቀፍ ወንጀል መጠየቅ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው የህውሃት ቡድን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል   ህዝብ ላይ እየፈፀመው የሚገኘውን ሽብር ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል።

ወይዘሮ መስከረም ተክለሃይማኖት በሰጡት አስተያየት፤ ሽብርተኛው ቡድን የትግራይን  ህዝብ ከሌላው እህት ወንድሞቹ ለመነጠል የሚያደርገውና ትውልዱን ለማጥፋት የሚፈፅመው  በአለም አደባባይ በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቀው መሆኑን ነው ያመለከቱት።

"እኔም ሆንኩ ሌላው ትግራዋይ የህወሃትን የሽብር ቡድን በፅኑ እናወግዛለን፤ በተቀናጀ መንገድ ለህግ ለማቅረብ የተጀመረውን ዘመቻ እንደግፋለን"በማለትም ገልጸዋል፡፡

ሌላው አሰተያየት ሰጪ አቶ ሰናይ ሲሳይ በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት የነበረባቸውን  ህጻናት  ለጦር ማሰለፍ አለም አቀፍ ወንጀል በመሆኑ አሸባሪው ቡድን በአለም  የጦር ፍርድ መቅረብ እንዳለበት ተናግረዋል።

የአሸባሪ ህወሃት ርዝራዥመንግስት ያስተላለፈውን የተኩስ  አቁሙ ውሳኔ ለትግራይ ህጻናት፣ ሴቶችና አርሶአደሮች ብሎም ለኢትዮጵያዊያን ውሳኔውን ማክበር ነበረበት ነው ያሉት።

ቡድኑ ስልጣንን በአቋራጭ ለማግኘትና ኢትዮያጵን ለማፍረስ ሽብርተኛው  የሚፈጽመውን  ወንጀል የኮነኑት አስተያየት ሰጪው፤ ኢትዮጵያ ህብረቷንና ቅንጅቷን ይበልጥ አፅንታ የጀመረችውን ዘመቻ በማጠናከር የጥፋት  ቡድኑን  ለህግ ማቅረብ አለባት ብለዋል።

መንግስት የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ  አሸባሪውን ቡድን  ለህግ ለማቅረብ እየፈፀመ  በሚገኘው ዘመቻ የትግራይ ህዝብ ነቅቶ ከመንግስት ጎን መሰለፍ እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ እቁበማርያም በሪሁን ናቸው፡፡

አሸባሪው ቡድን የትግይን ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ለመነጠል የሚያደርገው  ሴራ ፍጹም ተቀባይነት የሌለውና አስነዋሪ ተግባር ብለውታል፡፡

"ድሬዳዋ ያለነው የትግራይ ልጆች ቤተሰቦቻችን ናፍቀውናል፤ በግዞት ተይዘውብናል፤  ህውሃት እየፈፀመ የሚገኘውን ወንጀል በፅኑ እናወግዛለን" ብለዋል፡፡

የትግራይን ህዝብ ለረሃብ፤ ጦርነት ዳግም የዳረገና ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳና  እንዲገዳደል በማድረግ ወንጀል እየፈፀመ የሚገኘውን አሸባሪ ቡድን ሁሉም ዜጋ ሊያወግዘው ይገባል ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አረጋሽ ንጉሴ ናቸው፡፡

"እኛ የትግራይ ተወላጆች በኢትዮጵያዊነታችን ፣በሀገር ወዳድነታችን የምንኮራና ለሀገር ሉአላዊነት  መከበር ግንባር ቀደም የሆንን ሰዎች ብንሆንም አሸባሪው ቡድን ሥልጣንን በአቋራጭ  ለማግኘት እየፈፀመ በሚገኘው ወንጀል አፍረናል" ነው ያሉት፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሁሉም የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን በመቆም እየደረሰበት ያለውን ሰቆቃ በአጭሩ እንዲቋጭ ኃላፊነቱን  መወጣት አለበት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም