ቀጥታ፡

የትግራይ ሕዝብ ለአሸባሪው ቡድን ልጆቹን ለጦርነት መስጠት የለበትም

ሐምሌ 24/2013(ኢዜአ) የትግራይ ሕዝብ ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጥቅም ልጆቹን ለጦርነት መስጠት እንደሌለበት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ አሸባሪው ቡድን የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ለመለየት እያደረገው ያለው ጥረት እንደማይሳካም ተናግረዋል፡፡

የአሸባሪው የህወሓት ቡድን አባላት ልጆቻቸውን በውጭ አገራት ምቹና ቅንጡ ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ የደሃውን የትግራይ ሕዝብ ልጆች ለጦርነት እየማገደ መሆኑንም ገልጸዋል።

የትግራይ ሕዝብ ተረጋግቶ እንዳይኖርና ሠብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርሰው በየዕለቱ የጦርነት ነጋሪት እየመታ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን ባለመስጠት ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን ሊታገል እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ቡድኑ በሕጻናት ላይ ላደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት ሊጠየቅ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

የህወሓት አሸባሪ ቡድን የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ወገኑ ለመነጠል እየፈጸመ ላለው ድርጊት ተባባሪ ባለመሆን ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ሕዝቡ ይህን አሸባሪ ቡድን በቃህ ሊለው ይገባል ነው ያሉት።

አሸባሪው ቡድን ለሕግ ይቀርብ ዘንድ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለሕጻናት አደንዛዥ ዕጽ በመስጠት ለጦርነት እየማገደ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ማስረጃዎች መውጣታቸው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም