እንደ ህዳሴው ግድብ ስኬት ሁሉ የሀገራችንን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮችን በአንድነት በመመከት መቀልበስ ይቻላል - ኢዜአ አማርኛ
እንደ ህዳሴው ግድብ ስኬት ሁሉ የሀገራችንን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮችን በአንድነት በመመከት መቀልበስ ይቻላል
ባህርዳር ሐምሌ 24/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እንደተሳከው ሁሉ ህልውናችን የሚፈታተኑ ችግሮችን በአንድነት በመመከት መቀልበስ ይቻላል ሲሉ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ተናገሩ።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ከሰባት ሺህ ሃምሳ ተማሪዎች ዛሬ ሲያስመርቅ ለእውቁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት የተገኙት ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ፤ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገራችሁን ከገጠማት ችግር ለማላቀቅ በየምትሰማሩበት የስራ መስክ ተግታችሁ ልትሰሩ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያጋጣማትን የውስጥና ውጭ ጠላት መቀልበስ የምትችለው ህዝቦቿ የቀደመ አንድነታቸውን እንደጥንት አባቶቻቸው አጠናክረው በጋራ በመታገል እንደሆነ አስረድተዋል።
ታላቁ የአትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት የመጠናቀቅ ሚስጥሩ ኢትዮጵያዊነት ነው፤ይህም ህልውናችን የሚፈታተኑ ችግሮችንም በአንድነት በመመከት መቀልበስ እንደሚቻል የሚያረጋገጥ ነው።
የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎችም በተለይ በየሰለጠኑበት የሙያ መስክ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች በማከናወን ሀገራቸውንና ሀዝባቸውን በቅንነትና ታማኝነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸውም ሚኒስትሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶክተር አስራት አፀደወይን እንደተናገሩት፤ የኮሮና ቫይረስ ያሳደረውን ጫና በመቋቋም ለምርቃት መብቃታችሁ ታላቅ ስኬት ነው።
በቀጣይ በየምትሰማሩበት የሙያ መስክ ሊገጥማችሁ የሚችለውን ፈተና በፅናት በመቋቋም ሀገራችሁ አሁን ከገጠማት ችግር ለማላቀቅ በቁርጠኝነት ልትሰሩ ይገባል ብለዋል።
በተለይ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን አለመግባባት ለመፍታት ዩኒቨሲቲው ከሱዳን ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በ"ስፔሻሊቲ እና በፒኤች ዲ " የትምህርት መስኮች ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ተማሪዎች ሲሆኑ ከመካከላቸውም 2ሺህ 765 ሴቶች ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ለእውቁ የኪነ ጥበብ ሰው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ የክብር ዶክትሬት የሰጠ ሲሆን የጎንደር ከተማ አስተዳደርም በስሙ የሚጠራ መንገድ እንደሰየመለት ታውቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓት የፌደራልና ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።