ኢትዮጵያውያን ለሕልውና ዘመቻው እያደረጉት ያለው ንቅናቄ የአሸባሪውን ህወሓት ሴራ ያከሸፈ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ለሕልውና ዘመቻው እያደረጉት ያለው ንቅናቄ የአሸባሪውን ህወሓት ሴራ ያከሸፈ ነው
አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን ለሕልውና ዘመቻው እያደረጉት ያለው ንቅናቄ የአሸባሪውን ህወሓት ሴራ ያከሸፈ ነው ።
የሲዳማ ክልል ለሕልውና ዘመቻው ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስረክቧል።
የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ 'አንዳንዶች ህወሓት አፈር ልሶ እንደተነሳ ያስባሉ ሲሉ ለኢዜአ ሲገለጹ ይህ እንደማይሳካ መላው ኢትዮጵያውያን ለሕልውና ዘመቻው እያደረጉት ባለው ንቅናቄ የአሸባሪው ህወሓትን ሴራ መክሸፉን ያመላክታል ብለዋል።
ለዚህ ትልቁ ማሳያ ደግሞ በመላ አገሪቷ ዜጎች ያለማንም ቀስቃሽ ለሠራዊቱ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ የመጣባቸውን ጠላት በተባበረ ክንድ የመመከት ልምድ አላቸው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፤ በመላ አገሪቷ እየታየ ያለው ሕዝባዊ ንቅናቄ የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ንቅናቄው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በሕልውና የመጣበትን ጠላት በተባበረ ክንድ ለመመከት ወደኋላ እንደማይል ዓለምአቀፉም ማኅበረሰብ በመረዳት እጁን ከኢትዮጵያ ላይ ሊያነሳ ይገባል ብለዋል።
የሲዳማ ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ኤልያስ ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ እንቅስቃሴ የሚያሰጋቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች ከፍተኛ ጫና እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዘወትር ሲያደርገው እንደነበረው የአገሪቷን ሕዝቦች በብሄርና በኃይማኖት በመከፋፈል ታላቋን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየሞከረ ነው ብለዋል።
ይሁንና የአሸባሪ ቡድኑ ኢ-ሠብዓዊ ድርጊቶች መላ ውን የአገሪቷን ሕዝብ አንድነት በማጠናከር ቡድኑን እስከመጨረሻው ለማጥፋት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲረባረብ አድርጓል ነው ያሉት።
ከ4 ሺህ በላይ የክልሉ ወጣቶች የሕልውና ዘመቻውን መቀላቀላቸውን ጠቅሰው፤ አሸባሪው ቡድን እስከሚደመሰስ የክልሉ ነዋሪዎች ከሠራዊቱ ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
"የክልሉ ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ ጀመረ እንጂ አልጨረሰም" ያሉት አቶ አሸናፊ፤ ከ45 ሚሊዮን በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።
በመከላከያ ኅብረት ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ የፋይናንስ ሥራ አመራር ዳይሬክተርና የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል አስረስ አያሌው በበኩላቸው፤ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ቢያሳልፍም አሸባሪው ቡድን ከጥፋቱ አልተቆጠበም ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን ለኢትዮጵያም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ ምንም አይነት ኃላፊነት እንደማይሰማው በተደጋጋሚ አስመስክሯል ያሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ፤ ግብዓተ መሬቱን ለመፈጸም መላው ሕዝብ እየተረባረበ መሆኑን አክለዋል።
የትግራይ ሕዝብ የቡድኑን እኩይ ዓላማ በማውገዝ ለኢትዮጵያ አንድነት ድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የሲዳማ ክልል ከባለሃብቶችና ከኅብረተሰቡ ያሰባሰበውን 221 በሬ፣ 215 በግና 204 ፍየል ለመከላከያ ሚኒስቴር አስረክቧል።
በተጨማሪም 30 ሚሊዮን ብር ያስረከበ ሲሆን ድጋፉ አሸባሪው ህወሓት እስከሚጠፋ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል።
የትግራይ ሕዝብ አሸባሪውን ቡድን እስከመጨረሻው ለማጥፋት በሚደረገው ርብርብ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።