የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን ገፅታ እየቀየረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን ገፅታ እየቀየረ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአገሪቷን ገጽታ እየቀየረ መሆኑ ተነገረ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የተቋሙ ሠራተኞች ዛሬ በአዲስ አበባ ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ተገኝተው የፍራፍሬና ምግብ ነክ ያልሆኑ ችግኞችን ተክለዋል።
የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የችግኝ ተከላ "እንደ አገር ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ሥራ ነው" ብለዋል።
እየተከናወነ ያለው ኢትዮጵያን የማልበስ የችግኝ ተከላ ተግባርም "የኢትዮጵያን ገጽታ እየቀየረ ያለ መርሃ ግብር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
አረንጓዴ አሻራ ማኖር የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑን ጠቁመው፤ የተቋሙ ሠራተኞችም በዚህ መነሻ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ተናግረዋል።
የኢዜአ ሠራተኞች በተለያዩ አካባቢዎች በየዓመቱ ችግኞችን በመትከል እንክብካቤ እንደሚያደርጉና የተተከሉት ችግኞችም በጥሩ የጽድቀት ደረጃ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
የተቋሙ ሠራተኛ አቶ አዘነ በሱፍቃድ በበኩላቸው 'ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ አይደለም ተንከባክቦ ማፅደቅም ይገባል' ብለዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በተቋሙ በተካሄዱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች መሳተፋቸውን የገለጹት አቶ አዘነ፤ የተከሏቸውን ችግኞች እንደሚንከባከቡም ተናግረዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እዮብ እሸቱ በተያዘው ክረምት በወረዳ ደረጃ 103 ሺህ ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁንና እስካሁን ከዕቅዱ በላይ 105 ሺህ ችግኞች መተከላቸውንና በዚህም የፌዴራል ተቋማት፣ የኅብረተሰብ አደረጃጀቶችና የወረዳውን ነዋሪዎች ጨምሮ 78 ሺህ ሰዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
የተተከሉት ችግኞች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ ወረዳው የቅርብ ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
በ2013 ዓ.ም ክረምት በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።