በሐረሪ ክልል ያለውን ሰላም ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

76
ሀረር ነሃሴ 2/2010 በሐረሪ ክልል አሁን ላይ ያለውን የተረጋጋ ሰላም ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን የክልሉ ፍትህና ፀጥታ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ አበበ መብራቱ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በሐረሪ አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከትና ግርግር በክልሉም ለማንፀባረቅ የሚሞክሩ  ምልክቶች ታይተዋል፡፡ በዛሬው ዕለት የአካባቢውን ሰላም ሊያውክ የሚችል መልዕክት ያለበት ቲሸርት ለመሸጥ የሞከረ ግለሰብ  በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል። ዓላማው በግልፅ እስኪታወቅ ድረስ የቲ-ሸርቱ ሽያጭ እንዲቋረጥ መደረጉን አመልክተው በተለምዶ ሸዋበር በተባለው ስፍራ የግለሰብ ሆቴልን በእሳት ለማያያዝ የተደረገው ሙከራ መክሸፉንም አመልክተዋል፡፡ በክልሉ ሁከት የሚቀሰቅሱ ድርጊቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቢሮው ከመከላከያና ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ከአባገዳዎች፣ ወጣቶችና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም