ቀጥታ፡

መከላከያ ሠራዊትን በሙያችን ለማገዝ ተነሳስተናል

አሶሳ፤ ሐምሌ 24/2013(ኢዜአ) ጁንታውን ለማስወገድ በግንባር ከሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ተነሳስተናል ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ።

የጤና ባለሙያዎቹ በግንባር ካለው ሠራዊት ጎን በመሰለፍ በውትድርና ሙያ ጭምር ለማገልገል ተዘጋጅተዋል፡፡

ዶክተር ታከለ ሽፈራው ከክልሉ የጤና ባለሙዎች መካከል አንዱ  ሲሆኑ የመከላከያ ሠራዊት ለሀገር ደህንነት መሠረት መሆኑን ለኢዜአ ተናገረዋል፡፡

"ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት የሌለው ሀገር አጥር የሌለው ቤት ማለት ነው" ያሉት  ዶክተር ታከለ፤ ሠራዊቱ  ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ህዝቡ ከጎኑ ሆኖ እያደረገ ያለውን የደጀንነት ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

"በጤና ሙያችን ተቀጥረን ህዝብን እያገለገልን ያለነው መከላከያ ሠራዊቱ ለሀገር ሠላም ህይወቱን ጭምር እየሰዋ በመሆኑ ነው" ብለዋል፡፡

ሠራዊቱ በአሁኑ ወቅት ለሃገር እየከፈለ ባለው መስዋዕትነት ጉዳት ሲደርስበት በስፍራው ተገኝቶ ማከም የጤና ባለሙያው ሙያዊ ሃላፊነት መሆኑንም ዶክተር ታከለ ገልጸዋል፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድንና አጋሮቹ የሀገሪቱን የእድገት ጉዞ ለመቀልበስ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጤና ባለሙያ አቶ ግርማ ሙሉነህ ናቸው።

"ቡድኑ የሚከተለው እኔ ካልመራሁ ሀገር ትፍረስ የሚል የተሳሳተ አካሄድ በሀገር ላይ ካጋጠመ ክፉ ወረርሽኝ ባልተናነሰ ሁኔታ የሚታይ ነው" ብለዋል።

የጤና ባለሙያው ኢትዮጵያ በየትኛውም ጊዜ በሚሸረብባት ሴራ ተደናቅፋ ወደኋላ የተመለሰችበት ጊዜ አለመኖሩንም አመልክተዋል።

የህክምና ባለሙያዎች ስራቸው ወደጤና ተቋም የመጡ ሕሙማንን ማከም ብቻ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ግርማ፣ ከሠራዊቱ ጎን በግንባር ተሰልፈው ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት መነሳሳታቸውን አረጋግጠዋል።

"ሀገራችን የተደቀነባትን አደጋ ለመቀልበስ የመንግስትን ጥሪ ብቻ እየጠበቅን ነው" ያሉት ደግሞ ሌላው የክልሉ ጤና ባለሙያ አቶ ገመቹ ቶሎሳ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሠላም እስኪመለስ ድረስ መንግስት በሚፈልገው ሁሉ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ሀገራቸውን በውትድርና ማገልገላቸውን የገለጹት አቶ ደመቀ ሽፈራው በበኩላቸው፣ አሁንም በጤና ሙያ ለሽልማት ያበቃ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" የሚል አስተሳሰብ የያዘው አሸባሪው ህወሓት ሃገር እንዳትረጋጋ በማድረግ ወደ ቀውስ መክተት ዋነኛ ግቡ መሆኑንም ገልጸዋል።

"ቡድኑ ሴረኛ መሆኑን ሀገርን ለ27 ዓመታት በበላይነት ሲመራ በተጨባጭ አሳይቷል" የሚሉት አቶ ደመቀ፣ ይህንን የኢትዮጵያ ህዝብም ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ይህ ጥረቱም አይሳካለትም" ብለዋል።

ሃገር ሠላም እንድትሆንና አንድነቷ እንዲረጋገጥ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ሀላፊነት የጎላ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

በግንባር ካለው ሠራዊት ጎን በመሰለፍ በውትድርና ሙያ ጭምር ሀገራቸውን ለማገልገል መነሳሳታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሮናን በመከላከሉ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ ላደረጉ የጤና ባለሙያዎች  ትናንት  እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም