ቀጥታ፡

''የምዘምተው አገሬ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም እንድትኖር ነው!''

ሐዋሳ ሐምሌ 23/2013(ኢዜአ)''የምዘምተው አገሬ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም እንድትኖር ነው!''

ይርጋለም ከተማ የመጣው ወጣት አንዳርጌ ዮሴፍ የአገሩ አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል የወሰነው  የእናት ጡት ነካሽ የሆነውን ጁንታ ለማስወገድ መሆኑን ይናገራል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር እንደ ቀደምት ትውልዶች መስዋዕትነት እንከፍላለን እንጂ፤ በየትኛውም ኃይል  አገራችን አትፈርስም ከሚሉት የሲዳማ ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት ዮሴፍ በውትድርና ሙያ አገሩን ለማገልገል በሙሉ ፈቃደኝነት መነሳቱን ከጓደኞቹ ጋር ዛሬ  በሐዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ በተዘጋጀው የሽኝት ሥነ ሥርዓት ለኢዜአ ገልጿል።  

የእናት ተምሳሌት የሆነችው አገሩ መደፈሯ ስለሚያንገበግበው ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም እንድትኖር ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን ተናግሯል።

ወጣት በነበሩ ሙሉጌታ እንደሚለው አገሩን ከውጭ ጠላት ጋር በመመሳጠር  ለማፍረስ የተነሳውን ጁንታ ለማስወገድ በቁጭት ተነስቷል።

በዘመነ አገዛዙ ወጣቱን ሥራ አጥ ከማድረግ ባለፈ  አገሪቷን ሲበዘብዝና ልማቷን ሲያደናቅፍ የቆየው ቡድን የተመልሶ  ለመምጣት የሚያደርገውን  መፍጨርጨር  ለመታገል ቆርጦ መነሳቱን ነው የገለጸው።  አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ በሚያደርጉት  ትግል የኢትዮጵያ ሕዝብ  በሞራል  እንዲደግፋቸውም ጠይቋል።

የጁንታውን ሴራና ጥቃት ለማክሸፍ ብሎም የአገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር መከላከያ  ሠራዊቱን ለመቀላቀል መወሰኑን የተናገረው ደግሞ  ወጣት ብሌን ሃይሶ ነው።

በሥልጣን ዘመኑ ብዙ ዘግናኝ ግፎችን በዜጎች ላይ የፈጸመው ጁንታ፤ ለተጨማሪ ጭካኔ መነሳቱ እንዳበሳጨው የገለጸው ወጣቱ ዘማች፣ "አሸባሪው ቡድን አገርን ለመበታተን እያደረገ ያለውን  ሴራ ፣ተንኮልና ግፍ  ለማስቀረት እፋለማለሁ" ብሏል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ወጣቶቹ አገራቸውንን ከውስጥና ውጭ ጠላቶች ለመታደግ በከፍተኛ አገራዊ ስሜት ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት ለመቀላቀል ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

ጁንታው አገሪቱን ሲመራ በቆየባቸው 27 ዓመታት በተለያዩ መንገዶች ዘረፋ ከመፈጸሙ ባሻገር፣ የሕግ የበላይነትን መጣሱን ገልጸዋል።

የትግራይ ሕዝብ ጁንታው በእሳት እየማገደው መሆኑን አውቆ ትግሉን ከኢትዮጵያውያን ጋር በማቀናጀት ነጻነቱን እንዲያውጅ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ወጣቶቹ ለእናት አገራቸው አለኝታ  እንዲሆኑ በማሳሰብ የኢትዮጵያ  ሰንደቅ ዓላማን በማስረከብ ሸኝተዋቸዋል።

የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ባለሀብቶችና  ሕዝብ ለአገር መከላከያ ሠራዊት አለኝታነቱን ለማሳየት 30 ሚሊዮን ብር ፣ ከ600 በላይ የእርድ እንስሳትና ስንቅ ድጋፍ ማድረጋቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም