ቀጥታ፡

"ሕዝብ ለሕዝብ" የኪነት ቡድን ዳግም ሊቋቋም ነው

ሐምሌ 23/ 2013 ዓ.ም(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ብዝሃ-ማንነቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተዘዋውሮ ያስተዋወቀው "ሕዝብ ለሕዝብ" የኪነት ቡድን ዳግም ሊቋቋም መሆኑን ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ መነሻ በማድረግ የተቋቋመውና "ሕዝብ ለሕዝብ" የተሰኘው የኪነት-ቡድን የኢትዮጵያን ህብረ-ብሔራዊነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ረገድ ተጠቃሽ ነው።

የኪነት ቡድኑ ዋንኛ ዓላማ  በወቅቱ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ  በነበረው አስከፊ የረሃብ አደጋ  የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላደረገው ነፍስ የማዳን እርዳታ ምስጋና ማድረስና የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ማስተዋወቅ ነው።

የስመ-ጥር የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን እውቀት፣ልምድና የፈጠራ ችሎታ የተጠቀመ፤ በተሳታፊዎች ቁጥር፣ በህብረ-ትርኢቱ አይነትና ድምቀት እንዲሁም በአልባሳትና በመድረክ ዝግጅቱ በኢትዮዽያ የኪነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው።

በእንግሊዝኛ፣ ጣሊያንኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛና በሌሎች ቋንቋዎች የሚታተሙ የተለያዩ ሀገራት  ጋዜጦችም ስለ ኪነት ቡድኑ በስፋት እንደጻፉ ይነገራል።

የኪነት ቡድኑ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድ ውጤታማ ስራ መስራቱም እንዲሁ።

አያልነህ ሙላቱ፣ ደበበ ሰይፉ፣ አፈወርቅ ተክሌ፣ ተስፋዬ ለማ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ታደሰ ወርቁና ሌሎች ስመ-ጥር የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች ይዞ የተመሰረተው "ሕዝብ ለሕዝብ" የኪነት ቡድን፤ ከ30 ዓመታት በኋላ ዳግም ሊቋቋም መሆኑ ተነግሯል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በተለይም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ተቋርጦ የነበረውን ህዝብ ለህዝብ ኪነ ጥበባዊ ስራ ዳግም ወደስራ ለማስገባት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።

ሕዝብ ለሕዝብ ኪነት ቡድን እንደገና ለማቋቋም ረዥም ጊዜ የወሰደ ጥናት መደረጉን ገልጽው፤ የኪነት ቡድኑ አባል የነበሩየኪነ ጥብብ ሰዎች ያሉበት ኮሚቴ ዳግም ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ለኪነት-ቡድኑ በጀት መያዙንም ሚኒስትር ድኤታዋ ገልጸዋል።

የቅድመ ስራዎች ሲጠናቀቁም ኪነት ቡድኑ በሀገር ውስጥ ከተሞች፣ በአፍሪካና በዓለም መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ባህልና እሴት የማስተዋወቅ ስራ እንደሚያከናውን ጨምረው ገልጸዋል።

የኮሚቴው አባልና የዜማና ግጥም ደራሲው ሀብታሙ ቦጋለ የኢትዮጵያን ባህላዊ ትውፊቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ አዳዲስና ነባር ስራዎችን የማደራጀት ተግባር መጀመሩን ተናግረዋል።

"ሕዝብ ለሕዝብ" ቁጥር ሁለት ከመጀመሪያው በተሻለ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም