አሸባሪው ህወሃት በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመው ግፍ ከዕለት ተዕለት እጅግ እየከፋ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመው ግፍ ከዕለት ተዕለት እጅግ እየከፋ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2013(ኢዜአ) የመከላከያ ሠራዊት ከመቀሌ ከወጣ በኋላ አሸባሪው ህወሃት በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመው ግፍ ከዕለት ተዕለት እጅግ እየከፋ መምጣቱን ጋዜጠኛ አርዓያ ተስፋማርያም ተናገረ።
ጋዜጠኛ አርዓያ ተስፋማርያም ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለጸው፤ አሸባሪው ህወሃት በትግራይ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለው አሰቃቂ ግፍ ዕለት ተዕለት እየጨመረ መጥቷል።
አሸባሪው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት መንግሥት ወደ ህግ ማስከበር እርምጃ መግባቱ ይታወሳል።
ይህን እርምጃ ተከትሎም መንግስት በክልሉ የጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ሁኔታዎችን ወደ ቀድሞው ለመመለስ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለፌዴራል መንግስት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ባቀረበው ጥያቄ መሰረትም ለትግራይ ህዝብ ጥቅምና የጥሞና ጊዜ ሲባል መንግስት ጥያቄውን መቀበሉ ይታወሳል።
መንግሥት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሸባሪው ህወሃት እንደ እድል ተጠቅሞ የትግራይ አርሶ አደር ለእርሻ ሥራና ለሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያውለው ለማድረግ አልቻለም።
ይልቁንም አሸባሪ ቡድኑ አፍራሽ ሥራ ውስጥ በመግባት በትግራይ ሕዝብ ላይ በደል እየፈጸመ ይገኛል።
የመከላከያ ሠራዊት ከወጣ በኋላ የሽብር ቡድኑ በህዝቡ ላይ አሰቃቂና ዘግናኝ ተግባራት እየፈጸመ መሆኑን ነው የገለጸው።
አሸባሪ የህወሃት ቡድን የትግራይ ተወላጆችን "የጊዜያዊ አስተዳደር አባላት ናችሁ" እንዲሁም "የመከላከያ ሠራዊቱን ቀልባችኋል" እና ሌሎች ምክንያቶችን በመደርደር የክልሉን ተወላጆች እየገደለ መሆኑንም አብራርቷል።
ቡድኑ እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ ከ450 በላይ ንጹሃን የገደለ ሲሆን፤ በውቅሮ፣ በአክሱምና በሌሎች አካባቢዎች በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ያተኮረ ጥቃት መሰንዘሩንም ነው ያብራራው።
አሸባሪ ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ ወንድም ከሆኑት የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ለማጋጨት የተለያዩ ሴራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም አንስቷል።
ቡድኑ አሁን ላይ የትግራይ ሕዝብ ከአማራና አፋር ህዝቦች ጋር እንዲጋጭ ተከታታይ ትንኮሳዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግሯል።
በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ "አሸባሪ ቡድኑ በሚለኩሰው እሳት ሰለባ እምሆነው እስከ መቼ ነው?" ብሎ መጠየቅ እንዳለበትም ጠቁሟል።
ቡድኑ የትግራይ ህጻናትን ወደ ጦርነት በማሰማራት "ለትግራይ ህዝብ ዴንታ የሌለው መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው" ብሏል።
ሰሞኑንም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ እድሜያቸው ከ9 እስከ 12 የሚሆኑ ህፃናትን ከመቀሌ ከተማ ሰብስቦ መውሰዱን ከስፍራው መረጃ እንደደረሳቸውም ተናግሯል።
"የአሻባሪ ቡድኑ ቁንጮ መሪ ልጆች ግን በተለያዩ አገሮች የተንደላቀቀ ህይወት እየኖሩ መሆኑን የትግራይ ህዝብ ሊገነዘብ ይገባል" በማለትም ጠቅሷል።
ከዚህም አልፎ አሸባሪ ቡድኑ የእርዳታ እህል ወደ ክልሉ እንዳይገባ ማስተጓጎሉ ደግሞ ቡድኑ በችግር ውስጥ ላለው የትግራይ ህዝብ ምንም እንደማይገደው ያመላክታል ነው ያለው።
አሁን ላይ በክልሉ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የጠቀሰው ጋዜጠኛ አርዓያ፤ ከዚህ አኳያ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው ወደ አጎራባች ክልሎች እየሄዱ መሆኑን ተናግሯል።
አሸባሪ ቡድኑ የእርዳታ እህል የሚጓጓዝባቸውን መንገዶች በከባድ መሳሪያ በመደብደቡ 170 ተሽከርካሪዎች በአፋር ክልል ሠመራ መቆማቸው መዘገቡ ይታወሳል።