በሀዋሳ ከተማ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ ከተማ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ
ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 23/2013(ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የገመጦ ቱላ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማሻሻያ ፕሮጀክት ግንባታ ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ ።
የከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በምረቃው ሥነ ሥርዓት እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በቱላ ክፍለ ከተማ ስድስት ቀበሌዎች የሚገኙ ከ81 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋል።
ፕሮጀክቱ በቀን ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሊትር በላይ ውሃ በማመንጨት በ19 ቦኖዎች አማካይነት ለነዋሪዎቹ እንደሚያከፋፍል አስረድተዋል።
ከአምስት ዓመታት መስተጓጎል በኋላ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የመልካም አስተዳደር ችግር ለማቃለል በወሰደው አቋም የፕሮጀክቱ ግንባታ ለፍጻሜ መብቃት መቻሉን ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የውሃ ፕሮጀክት የለውጡ መንግሥት ለሕዝብ የልማት ጥያቄ ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ አንዱ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በሥልጣን ጥም የሰከረው አሸባሪው የወጠነውን ሀገር የማፍረስ ድርጊት መመከት ይገባል ብለዋል።
አሸባሪውን ቡድን በመጠቀም የተለያዩ ጫናዎች ለመፍጠር የሚሞክሩ ምዕራባዊያንና ሌሎች እጃቸውን ከእኛ ላይ እንዲያነሱ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባናል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ታደለች ባርጉዳ በሰጡት አስተያየት፤ ንጹህ መጠጥ ውሃ ፍለጋ እስከ አምስት ኪሎ ሜትር በመጓዝ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ሲያጠፉ እንደነበር አስታውሰዋል።
ፕሮጀክቱ ተጀምሮ በመቆሙ ተስፋ ቆርጠው እንደነበር ጠቁመው፤ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት በመጠናቀቁ ተደስቺያለሁ ብለዋል።።
በምረቃው ሥነ ሥርዓት የሲዳማ ክልልና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ከሥስፋር ዘግቧል።