ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በኦንላይን ቼስ ኦሊምፒያድ የሚወክሉ ስፖርተኞች ተመረጡ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ23/2013 (ኢዜአ) በሁለተኛው የኦንላይን ቼስ ኦሊምፒያድ በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ 12 ስፖርተኞች ተለይተዋል።

ዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን /ፊዴ/ ያዘጋጀው ሁለተኛው የኦንላይን ቼስ ሻምፒዮና ከነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ መስከረም 5 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።

በቼስ ኦሊምፒያዱ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈውን ብሔራዊ ቡድን ለመምረጥ ከሐምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በቶርኔሎ ፕላትፎርም ሲካሄድ የቆየው ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።

ውድድሩ በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች፣ ከ20 ዓመት በታች ወንዶችና ሴቶች ዘርፍ ተከፋፍሎ ተካሄዷል።

ራፒድ በሚል በሚጠራውና ለ15 ደቂቃ በሚቆየው የቼስ ውድድር አይነት የተደረገው የማጣሪያ ውድድር 53 ተወዳዳሪዎች መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በማጣሪያ ውድድሩ በተመሳሳይ በወንድም በሴትም ስድስት ተወዳዳሪዎች በድምሩ 12 ስፖርተኞች መመረጣቸውን ተናግረዋል።

በአዋቂ ወንዶች አሸናፊ ሙሉጌታ፣ ይማም አበራ፣ ደበላ ፈቀዳና አዲስዓለም ተመስገን እንዲሁም በአዋቂ ሴቶች ሲና ታደሰ፣ መቅደስ ደምሴ፣ ማሾ በየነና ልደት አባተ ተመርጠዋል።

ከ20 ዓመት በታች ወንዶች ማርኪ እንድሪያስና ዮሴፍ ክፍሌ የተመረጡ ሲሆን፤ ሳምራዊት ግርማና ቢታኒያ ኤርሚያስ ኢትዮጵያን ወክለው በኦንላይን ቼስ ኦሊምፒያድ ይሳተፋሉ።

በራፒድ የቼስ ኦሊምፒያድ ውድድሩ 94 ተወዳዳሪዎች የተመዘገቡ ቢሆንም በኢንተርኔት መቆራረጥና ኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ምክንያት መሳተፍ የቻሉት 53 ናቸው ብለዋል አቶ ሰይፈ።

ሁለተኛው የኦንላይን የቼስ ኦሊምፒያድ የሚካሄደው በራፒድ የቼስ ውድድር አይነት መሆኑን ጠቁመዋል።

በተያያዘ ዜና ብሊትዝ በሚል የሚጠራውና አምስት ደቂቃ በሚቆየው የቼስ የውድድር አይነት አገር አቀፍ የቼስ ሻምፒዮና ነገና ከነገ በስቲያ እንደሚካሄድም ገልጸዋል።

በራፒድና በብሊትዝ የቼስ ውድድር በወንዶች ከ1 እስከ 15 በሴቶች ከ1 እስከ 8 ለወጡ ተወዳዳሪዎች የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን 23 ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት አዘጋጅቷል።

እ.አ.አ 2020 በሩሲያ አስተናጋጅነት 44ኛውን የቼስ ኦሊምፒያድ ለማዘጋጀት እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን ውድድሩን ማራዘሙ የሚታወስ ነው።

ይሁንና ፌዴሬሽኑ በአካል የሚካሄደው ውድድር እስከሚጀመር ውድድሩን ለማስቀጠል የኦንላይን ቼስ ኦሊምፒያድ እ.አ.አ 2020 ለመጀመሪያ ጊዜ አካሄዷል።

በኦሊምፒያዱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ163 ብሔራዊ ቡድኖች የተወጣጡ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች ተካፍለዋል።

በሁለቱም ጾታዎች ሩሲያና ሕንድ ለፍጻሜ ቢደርሱም በጨዋታው ወቅት ባጋጠመ የሰርቨር ብልሽት ምክንያት ሕንድና ሩሲያ የውድድሩ የጋራ አሸናፊ በሚል የወርቅ ሜዳሊያ እንዲያገኙም ተደርጓል።

ኢትዮጵያ በቼስ ኦሊምፒያዱ በተመሳሳይ በሶስት ወንድና ሴት ተወዳዳሪዎች ተወክላ የተሳተፈች ሲሆን ተወዳዳሪዎቹ ከነበሩበት ምድብ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻሉም።

የሁለተኛው የኦንላንይን ቼስ ኦሊምፒያድ ልክ እንደ መጀመሪያው ውድድር በChess.com ሰርቨር አማካኝነት የሚካሄድ ነው።

የቼስ ኦሊምፒያድ በዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን አማካኝነት እ.አ.አ ከ1927 ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም