ከሶስት ዞኖች ለህልውና ዘመቻው ከ159 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ከሶስት ዞኖች ለህልውና ዘመቻው ከ159 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ
ደብረ ብርሃን/ ደሴ/ ደብረ ማርቆስ ሐምሌ 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ፣ ደቡብ ወሎና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች ለህልውና ዘመቻው በጥሬ ገንዘብ ብቻ 159 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተሰበሰበ።
የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ታየ ለኢዜአ እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝቦችን አንድነትና አብሮነት ለማስቀጠል የተጀመረው የህልውና ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነዋሪው ድጋፍ እያደረገ ነው።
ከዞኑ ህዝብ ለህልውና ዘመቻው ከ532 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት በጥሬ ገንዘብ 95 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ነዋሪው በአይነት 12 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
የተሰበሰበው ድጋፍ በግንባር ለሚገኘው የጸጥታ ሀይል መላኩን ጠቁመው የድጋፍ ማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደርም በጥሬ ገንዘብ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማሰብሰቡን አስታውቋል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ እንዳሉት ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ472 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለመሰብሰብ ታቅዶ በተደራጀ አግባብ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
እስካሁን ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቁመው የመንግስት ሰራተኛውም የወር ደመወዙን ለመስጠት ቃል መግባቱን አስታውቀዋል።
ሀገር ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳውን ጁንታ ለመመከት ሁሉም የሚችለውን በማድረግ ሀገራዊ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ምክትል አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ በምስራቅ ጎጃም ዞን ለህልውና ዘመቻው 500 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሃብት ለማሰባሰብ እየተሰራ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የዞኑ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ታደሰ አለማየሁ አስታውቀዋል።
እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ 19 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ጠቁመው 307 ሚሊዮን ብር ደግሞ ቃል መገባቱን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በሃገር ህልውና ላይ የተደቀነው የህውሃት አፍራሽ ቡድን ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ የደጀንነት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።