የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በአገር ማዳን ትግሉ በመሳተፍ ደማቅ ታሪክ እንዲጽፉ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በአገር ማዳን ትግሉ በመሳተፍ ደማቅ ታሪክ እንዲጽፉ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 23/2013 ( ኢዜአ) የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በአገር ማዳን ትግሉ በመሳተፍ ደማቅ ታሪክ እንድትፅፉ አደራ እላለሁ ሲሉ ብርጋዴር ጀኔራል አስፋው ማመጫ ተናገሩ።
በሕልውና ዘመቻ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሚና ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ብዙነሽ መሰረትን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ወታደራዊ መኮንኖች እንዲሁም የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች በመድረኩ ታድመዋል።
የኢትዮጵያ የጥበብ ሰዎች አገር ስትደፈር፣ የህልውና አደጋ ሲጋረጥባት እንደ መክሊቶቻቸው ተጫውተዋል፣ ዘፍነዋል፣ ፅፈዋል በዚህም ጉልህ ሚና አበርክተዋል።
የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ተወካይ ብርጋዴር ጀኔራል አስፋው ማመጫ ኪነ-ጥበብና መከላከያ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፣ መከላከያ ለኪነ-ጥበብ ትልቅ ስራ ሰርቷል፤ ስመጥር የጥበብ ሰዎችንም አፍርቶ ለአገር አብቅቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በገጠሟት ፈተናዎች እያሸነፈች ስትመጣ ጠላቶች እንዲወድቁ፤ አገር ድል እንድትነሳ ኪነ-ጥበብ ትልቅ ሚና ነበረው ሲሉም ተናግረዋል።
ጀግንነት፣ አርበኝነት፣ የአገር ፍቅር ምንነት እንዲሁም የኢትዮጵያ ተዋግቶ ማሸነፍ ባሕል እንዲሆን ኪነ- ጥበብ ትልቅ ሚና ነበረው ያሉት ብርጋዴር ጀኔራሉ፤ ለጥንት አባቶች ድል መንሳት በየዘመኑ የነበሩ የኪነ ጥበብ ሰዎች ጉልህ ሚና ነበረው ብለዋል።
በቅርቦቹ የአገር ወረራ ክስተቶች ለአብነት በሶማሊያ ወረራ ወቅት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የነበራቸውን ጉልህ ሚናም አውስተዋል።
የወቅቱ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችም አገር ለማዳን በሚከፈል መስዋዕትነት እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ አድንቀው፣ በቀጣይም እንደ ቀደምት የጥበብ ባለሙያዎች አገር ለማዳን በሚደረገው ትግል በመሳተፍ ደማቅ ታሪክ እንዲፅፉ አደራ ብለዋል።