ቀጥታ፡

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ከጠብ አጫሪነት ድርጊቱ እንዲታቀብና የሰብአዊ ዕርዳታን እንዳያስተጓጉል ግፊት እንዲያደርግ ተጠየቀ

ሐምሌ 22/2013(ኢዜአ) የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ከጠብ አጫሪነት ድርግቱ እንዲታቀብና የሰብአዊ ዕርዳታን እንዳያስተጓጉል ግፍት እንዲያደርግ ተጠየቀ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ጋርኖ ጋር በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በበይነ መረብ ተወያዩ፡፡

በካናዳና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ረጅምና ታሪካዊ ግንኙነት በማንሳት ፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ወዳጅነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡

የካናዳዉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ጋርኖ የሀገራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ለውጥ ውይይት ማድረጋቸውንና የካናዳ መንግስት ለውጡን እንደሚደግፍ መግለጻቸውን አስታውሰዋል፡፡

በትግራይ ክልል ስላለው ፖለቲካዊና ሰብአዊ ሁኔታ በተመለከተ ካናዳ የሰብአዊ ዕርዳታ እንዲደርስ የምትፈልግ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የሰብአዊ ዕርዳታ ወደ ክልሉ እንዲዳረስ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ያሳለፈ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደመቀ ፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ግን ሰላማዊ መንገድን ከመከተል ይልቅ የዕርዳታ መተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋት በአማራና በአፋር ክልል አዲስ ትንኮሳ መክፈቱን አስረድተዋል፡፡

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ መንግስት በክልሉ ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር እንዲሁም ሲያደርግ የቆየውን የሰብአዊ ድጋፎች ዕውቅና ከመስጠት መቆጠቡ ፤ኢትዮጵያን ያሳዘነ ተግባር መሆኑንም አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡

ካናዳን ጨምሮ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰብአዊነት ላይ የተመሰረተውን የተኩስ አቁም ውሳኔን ቡድኑ እንዲያከብር ጫና እንዲደረግበት እና የቡድኑ የጥፋት ድርጊቶች እንዲወገዙም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

አሸባሪው ቡድን በከፈተው አዲስ ግጭት ምክንያት ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ስለተፈናቀሉ ሁለት መቶ ሺህ ዜጎች ሁኔታም የአለም አቀፍ ማህበረሰቡን ሊያሳስበው እንደሚገባም መናገራቸውን የወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።

በመጪው መስከረም ወር የሚመሰረተው አዲስ መንግስት ሁሉን አቀፍ ውይይት ለማካሄድ ዕቅድ እንዳለው ጠቁመው ፤ ህጻናትን ጭምር ወደ ጦርነት እያሰማራ እና በአዲስ አከባቢዎች ግጭት እየፈጠረ ያለው አሸባሪው ቡድን ድርጊቱን እንዲያቆም ማድረግ እንደሚገባም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚ/ር አቶ ደመቀ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም