የሲዳማ ክልል ባለሃብቶች ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት በተግባር እያሳዩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ክልል ባለሃብቶች ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት በተግባር እያሳዩ ነው
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 22/2013.(ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የሚገኙ ባለሃብቶች በግዳጅ ቀጠና ለሚገኘው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት በተግባር እያሳዩ ነው።
ባለሃብቶቹ ለሰራዊቱ ማጠናከሪያ ከ9 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ በሚሰጥበት ሁኔታ ከባለሃብቶቹ ጋር በሀዋሳው ሚሌኒየም አዳራሽ በተወያዩበት ወቅት የአድማስ ተስፋ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ አስቻለው አድማሱ በወቅቱ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ በአሸባሪው ህወሓት አይደናቀፍም።
ሀገራዊው ምርጫውና የህዳሴው ግድቡ ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ደግሞ የወደፊት ተስፋዋን የሚሳይና ወደ ስኬት የሚያንደረድር በመሆኑ በገጠመን ፈተና መረበሽ አይገባም ብለዋል።
በተለይ ነጋዴ ሰርቶ መበልጸግ የሚችለው ሀገር ሰላም ስትሆን በመሆኑ ሰላምን ለማስፈን ለሚታገለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚውል 200 ሺህ ብር ለግሰዋል።
ባለሃብቱ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉና አስፈላጊ ከሆነም እስከ ግንባር ድረስ ለመዝመት መነሳሳታቸውን አስታውቀዋል።
የእናት አገር ጥሪውን ተቀብዬ የድርሻዬን በማበርከቴ ኩራት ይሰማኛል ያሉት ደግሞ የይርጋለም ኮንስትራክሽን ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ይርጋለም አስፋው ናቸው። ድርጅታቸው 500 ሺህ ብር ለግሷል፡፡
የኤስ ኤም ጠቅላላ ንግድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ሮዲሶ በድርጅታቸውና በግላቸው 300 ሺህ ብር በመደገፍ ለሰራዊቱ አጋርነታቸውን ገልጸዋል።
በግንባር የተሰለፉትን መደገፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነትና ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው፣ እስከ ግንባር ለመዝመት ዝግጅ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለምትኖረው ሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ለሠራዊቱ ማጠናከሪያ 50 ሺህ ብር የለገሱት ደግሞ የቤቴል ሆሊ ዴንታል ክሊኒክ ሥራ አስኪያጅ ሲስተር መስከረም አበራ ናቸው።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤በህወሓት የስልጣን ዘመን ውስጣዊ ሞራላችንና አንድነታችን ተዳክሞ የቆየ ቢሆንም፤ አሁን እየታየ ያለው የአንድነት ስሜትና መንፈስ ኢትዮጵያን ወደፊት ያሻግራታል ብለዋል።
"ኢትዮጵዊነት በሥነ ልቦናና በነጻነት የኩራት ምልክት ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አሸባሪው ቡድን ያመጣው የመከፋፈል አደጋ ኢትዮጵያዊያንን ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ያሰለፈ በመሆኑ ባጠረ ጊዜ በድል እንደሚጠናቀቅ እምነታቸው ገልጸዋል።
ባለሃብቶቹ ድጋፉን በመስጠት ያሳዩት ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት የሚያኮራ ፤ የክልሉ መንግስትና ሕዝቡን በታማኝነት ያገለግላችኋል ብለዋል።