ዓለም አቀፍ ሕጎችን የተጻረረው ቡድን ምዕራባውያን ቸል ማለታቸው ሀገሪቱ እንድትዳከም ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው

ባህር ዳር ሐምሌ 22/2013 (ኢዜአ)ዓለም አቀፍ ሕጎችን የተጻረረው አሸባሪው የህወሃት ቡድን ምዕራባውያን ሀገራት በቸልታ ማለፋቸው ሀገሪቱ እንድትዳከም ካላቸው የቆየ ፍላጎት የመነጨ መሆኑን የህግ ምሁራን ገለጹ።
ህውሃት በስልጣን ዘመኑ ብሄርን ከብሄርና ሃይማኖት ከሃይማኖት በማጋጨት ስልጣኑን ለማጽናት በደል የፈጸመ አሸባሪ ቡድን ነው።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ ለኢዜአ እንዳስረዱት፤ ቡድኑ በአገዛዙ የተማረረው የኢትዮጵያ ህዝብ ታግሎ ያመጣውን ለውጥ በመቃወም መቀሌ ከገባ በኋላ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ጥቃትና በማይካድራ ያካሄደው ጭፍጨፋ አሸባሪነቱን በተግባር  አረጋግጧል።

በዚህም በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ በተካሄደው ወታደራዊ እርምጃ ወደ ዋሻ የገባው ቡድኑ መንግሥት ያስተላለፈውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔን በመጠቀም እያካሄደ ያለው ወረራ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

ድርጅቱ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የራሱን ፍላጎት ለማሳካት በሚፈጽመው እኩይ ተግባር አብዛኛውን የትግራይ ህዝብን ተጎጂ አደርጓል።

በትጥቅ ትግሉ ወቅት በህገ ወጥ መንገድ የጀመረውን የመሬት ማስፋፋት አሁን በአማራና አፋር ክልሎች በማካሄድ ሕዝቡ እያስጨረሰ ይገኛል።

ቡድኑ እንደ ሀገር ቢያስብ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኝ መሬትና ቦታ የሁሉም በመሆኑ አልምተን የምንጠቀምበትን መልካም እድል በስግብግብ ፍላጎቱ ባላጠፋው ነበር።

ቡድኑ ''የትግራይን ህዝብ ተጠቅተሃል'' በሚል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ህጻናትን፣ እናቶችንና አረጋውያንን በገፍ ለጦርነት በማሳለፍ እያስፈጃቸው መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ዓለም አቀፍ ሕጎችን የተጻረረው ቡድን ድርጊት አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራትና መገናኛ ብዙሃን ትኩረት አለመስጠታቸው የሚያስተዛዝብ እንደሆነ ነው ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ የጠቀሱት።

ዓላማቸውም ኢትዮጵያ እንድትዳከምና እንድትተራመስ ብሎም በእድገት ወደ ኋላ በመመለስ ህዝቦቿ በድህነት ተጎሳቁለው እንዲኖሩ ካላቸው የዘመናት ፍላጎት የመነጨ ነው።

“አሸባሪው ህውሃት አሁን እያሳየው ያለው መጠነ ሰፊ ወረራ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ይዞ የተነሳውን ግብ ለማሳካት ያለመ ነው” ያሉት ደግሞ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ደርሶልኝ የኔአባት ናቸው። 

በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከሉ በሰው ልጆች ላይ መፈጸም የማይገባቸው ወንጀሎችን በሙሉ አሸባሪው ቡድን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲፈጽም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቸልታ ማለፉ የሚያሳዝን ነው።

በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃትና በማይካድራ ላይ የተፈጸመውን የንጹሃን ጭፍጨፋ ከማውገዝ ይልቅ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸው ለእውነትና ለፍትህ ያልቆሙ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ያላቸው ምርጫ የውጭ ጫናን በመቋቋም የአሸባሪውን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ነው ብለዋል።

መንግሥት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔን ተከትሎ አሸባሪ ቡድኑ እየፈጸመ ያለው ወረራ የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያንን ጠላት አድርጎ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት ሕዝቡ በአንድነትና በጽናት መሰለፍ ይኖርብናል።

በሀገር አንድነትና ሉአላዊነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ መቀልበስ የሚቻለው ከአባቶቻችን የወረስነውን ጽናትና ጀግንነት መላበስም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም