ኢትዮጵያ የዓለም ቆዳ ልማት ጉባዔዎችን ለማስተናገድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዓለም ቆዳ ልማት ጉባዔዎችን ለማስተናገድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 22/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የዓለም የቆዳ ልማትና ቴክኖሎጂ ጉባዔዎችን ለማስተናገድ ዝግጅቷን በማጠናቀቅ ላይ እንደሆነ አዘጋጆቹ አስታወቁ።
የአፍሪካ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተቋም ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሕዳር 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሁለት ዓለም አቀፍ የቆዳ ልማት ጉባዔዎችን እንደሚያካሄድ አስታውቋል።
ጉባዔዎቹ አምስተኛው ዓለም አቀፍ የቆዳና 36ኛው ዓለም አቀፍ የቆዳ ቴክኖሎጂና ኬሚካል ባለሙያዎች ማኅበር ናቸው፡፡
የዓለም የቆዳ ጉባዔ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚካሄድ ሲሆን ከ300 በላይ ዓለምአቀፍ የዘርፉ ተመራማሪዎችና 50 አገራት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
በጉባዔው የቴክኖሎጂ አማራጮች፣ ጥናትና ምርምሮች በጋራ መስራት የሚያስችሉ ትስስሮች ላይ ምክክር ይደረጋል።
የአፍሪካ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች አማካሪ ፕሮፌሰር መኮንን ኃይለማርያም እንዳሉት፤ ጉባዔዎቹ በቆዳ ዘርፍ ልማት ሳይንስ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በዘርፉ ባሉ አማራጮችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።
ጉባዔው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም ለዓለም ለማሳየት፣ አቅም ካላቸው ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ጋር ትስስር ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ እንደሚጠቅማት ገልጸዋል።
ጉባኤውን እ.አ.አ ከመጪው ህዳር 1 እስከ 5 ለማስተናገድ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ እንደሆነ ገልጸዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረእየሱስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለቆዳና ቆዳ ውጤቶች ጥሬ እቃ አቅራቢ ብቻ ሳትሆን ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረት ወደ ዓለም ገበያ ለመድረስ እያከናወነች ያለውን ተግባር አስረድተዋል።
በመሆኑም ጉባዔው ኢትዮጵያ በቆዳ ዘርፍ ያላትን አቅምና ዘርፉን ለማልማት እያከናወነች ያለውን ተግባር ለዓለም ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላት ተናግረዋል።
የሞጆ ከተማን የቆዳ ዘርፍ ማዕከል በማድረግ ቆዳ ለሚገዙ ደንበኞች ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማቅረብና ከማጣሪያ ጀምሮ አጠቃላይ የምርት ሰንሰለቶችን በአንድ ቦታ ለማከናወን እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቆዳ ልማት ዘርፍ ያላትን አቅም በጉባዔው አጉልቶ በማሳየት ባለሃብቶችን፣ ገዥዎችን እንዲሁም አልሚዎችን ለመሳብ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍም በኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን በማስተዋወቅ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ለመሳብ ያግዛል ብለዋል።
በጉባዔው መሳተፍ የሚፈልጉ አካላት በአፍሪካ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተቋም ድረ-ገጽ ላይ የተቀመጠውን መስፈርት በማሟላት መሳተፍ እንደሚችሉ ተገልጿል።
በተጨማሪም እ.አ.አ ከታህሳስ 3 እስከ 6 ቀን 2021 የአፍሪካ አለም አቀፍ የቆዳ ወጤቶች አውደ ርዕይ በስካይ ላይት ሆቴል ይካሄዳል ተብሏል፡፡